የክልሉ ሕዝቦች ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በግድቡ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ለመመከት ዝግጁ ናቸው- አቶ አሻድሊ ሀሰን - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ሕዝቦች ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በግድቡ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ለመመከት ዝግጁ ናቸው- አቶ አሻድሊ ሀሰን
አሶሳ ጥቅምት 14/2013 ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝቦች ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ሆነው በግድቡ ላይ የሚሰነዘር ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን አስታውቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ያስተላለፉት የጥፋት መልዕክት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።
ይህም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚገዳደር በመሆኑ ለሚሰነዘር ጥቃት የሚታገስ እንደማይኖር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአባይ ጉዳይ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ ለመጠቀም በውይይት ላይ የተመሠረተ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ እየተከተለች መሆኑን አስታውሰዋል።
ግድቡ መላው ኢትዮጵያዊያን ያለ ልዩነት እየገነቡትና አሻራቸውን እያሳረፉበት ያለ የአንድነት መገለጫቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ለደህንነቱም በጋራ እንደሚቆሙም አቶ አሻድሊ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ እንደማይደራደሩ አመልክተው ታሪካችንም ለዚህ ዋነኛ ምስክር ነው ብለዋል።
የከልሉ ሕዝቦች ከሌሎች የኢትዮጵያ እህት ወንድሞቻቸው ጋር ሆነው በግድቡ ላይ የሚሰነዘር ማንኛውንም ጥቃት በመመከት ለማክሸፍ ዝግጁ መሆናቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።