ቀጥታ፡

አገርና ሕዝብን ከማንኛውም አደጋ መከላከል የሚያስችል ወታደራዊ አቅም አለን -- ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) አገርና ሕዝብን ከማንኛውም የውስጥና የውጭ አደጋ መከላከል የሚያስችል ሙሉ ወታደራዊ አቅም አለን ሲሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ። 

ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ይህንን የተናገሩት የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማዘዣ በአምስት ሻለቃ ያሰለጠናቸውን የኮማንዶ አባላት በብላቴ የጦር ማሰልጠኛ ማዕከል ሲያስመረቅ ነው።

ጄኔራል ብርሃኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገርና በሕዝብ ላይ ብጥብጥና ትርምስ ለመፍጠር እየሰሩ ያሉ የውጭና የውስጥ ኃይሎችን መመከት የሚያስችል ስልጠና፣ ትጥቅና የተሟላ አቅም አለን ብለዋል።

እነዚህ የሽብር አካላት አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳና ብጥብጥ እንዲፈጠር በማለም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሃያ በላይ ሁከት መፍጠራቸውንም ገልጸዋል።

አሁንም በጉራፈርዳ አካባቢ ይህንኑ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው ተግባሩን የሚፈጽሙት ከኢትዮጵያዊያን ግጭት ጥቅም ከሚያገኙ አካላት ጋር የሚያብሩ የውስጥ ኃይሎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ይህ ተግባር አይቀጥልም "በሠራዊቱና በሕዝቡ የጋራ ስራ እናመክነዋለን" ነው ያሉት።

ሠራዊቱን ዘለቄታዊ ባለውና የአገሪቷን ሉዓላዊነት በሚያስከብር መልኩ አጠናክረን እናደራጃለን ማለታቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም