አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀቱን አስታወቀ
አሶሳ፣ ጥቅምት 14 / 2013 (ኢዜአ) አሶሳ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
በአሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች በበኩላቸው ከየትኛውም አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎችን እንደልጆቻቸው በመቀበል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም እንዳሉት ተቋሙ በመጀመሪያ ዙር የዘንድሮ ተመራቂ የሚሆኑ አንድ ሺህ 700 በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል ተሰናድቷል፡፡
መማር ማስተማሩን የሚያስቀጥሉ፣ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚያስፈጽሙ እና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ስራን የሚከታተሉ ሶስት ኮሚቴዎች ተዋቅረው ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይ መማር ማስተማሩን ከኮሮና የጸዳ ለማድረግ የተማሪዎች ቁጥር በመማሪያ ክፍሎች ከ60 ወደ 25፣ በማደሪያ ክፍሎች ከስድስት ወደ ሁለት ለመቀነስ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን አስረድተዋል።
የመመገቢያ፣ ቤተ-መጻህፍት እና ቤተ-ሙከራዎች በጥንቃቄ ለውስን ተማሪዎች አግልግሎት ለመስጠት እንደተዘጋጁም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ለኮሮና ቫይረስ ህክምና የዋሉ የተወሰኑ የዩኒቨርሲቲው ክፍሎች በጸረ ተህዋሲያን መጽዳታቸውን ጠቁመው ይኸው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ከማል አስታውቀዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የተዘጋጀውን ሳኒታይዘር ጨምሮ ሌሎች ንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች መሟላተቸውን አመልክተዋል፡፡
ተማሪዎች ከዚህ ቀደም ለተግባራዊ ልምምድ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚያደርጓቸው ጉዞዎችን ለማስቀረት ቤተ-ሙከራዎችን በአስፈላጊ ቁሳቁስ ለማማሏት ጥረት መደረጉን ጠቅሰው የግቢው ኢንተርኔት ሽፋን 95 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተከታትለው በማጠናቀቅ እንዲመረቁ ለማድረግ መዘጋጀቱን ያመለከቱት ዶክተር ከማል ይህም ጫና እንዳያሳድር የተደራጀ የባለሙያዎችን ያካተተ መማክርት መሰናዳቱን አብራርተዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የምህንድስና ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር አሸብር በለጠ በበኩላቸው ተማሪዎች በቆይታቸው ተገቢውን እውቀት ይዘው እንዲወጡ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የኮሌጁ ቤተ-ሙከራ በአስፈላጊ ግብዓቶች በሚገባ መደራጀቱን ጠቁመው ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅተው እየተጠባበቁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አቀባበል ከማድረግ ጀምሮ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ ያለው ደግሞ የአሶሳ ከተማ ነዋሪው ወጣት ዮሴፍ አማረ ነው፡፡
አቶ መልካሙ ታደሰ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት አሶሳ አካባቢው ሠላማዊ እና የተረጋጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ወደ አሶሳ ሲመጡ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንደሚመጡ ማሰብ አለባቸው፤ ከየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚመጡ ልጆቻችን ናቸው ብለዋል፡፡
ኮሮናን በመከላከል ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀው እስኪመለሱ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነዋሪው ገልጸዋል፡፡
ከ10 በሚበልጡ ኮሌጆች እና የትምህርት ክፍሎች በ40 ዲፓርትመንቶች ትምህርት ሲሰጥ የቆየው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው በ2004 ዓ.ም መሆኑን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡