በአማራ ክልል የመማሪያ ክፍልና የግብዓት አቅርቦት ዕጥረት አጋጠመ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የመማሪያ ክፍልና የግብዓት አቅርቦት ዕጥረት አጋጠመ
ባህርዳር ጥቅምት 13/2013 (ኢዜአ) በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት በተሟላ መልኩ ለማስጀመር የመማሪያ ክፍልና የግብዓት አቅርቦት ዕጥረት እንደገጠመው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው ባጋጠሙ ችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ ከሲቪክ ማህበረሰብና ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር ዛሬ መክሯል።
በምክክር መድረኩ የቢሮው ኃላፊው ዶክተር ይልቃል ከፍአለ እንዳሉት ኮሮናን በመከላከል ተቋርጦ የቆየውን የመማር ማስተማር ስራ ለማስቀጠል ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
ሆኖም በትምህርት ዘመኑ ከ6 ሚሊዮን በላይ የአንደኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ኮሮናን በመከላከል ለማስተማር የክፍልና የወንበር እጥረት ማጋጠሙን ገልጸዋል።
ችግሩ ያጋጠመው በአንድ ክፍል መማር ያለበት የተማሪ ቁጥር በመወሰኑ በየትምህርት ቤቶቹ ያሉት ክፍሎች ከተማሪው ቁጥር ጋር መመጣጠን ባለመቻላቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል።
አዲስ የተገነቡ 51 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 5 ሺህ 464 ተጨማሪ ክፍሎች ወደ ስራ ቢገቡም እንዳልበቁ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአፍ አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ፣ ሳኒታይዘር፣ ፈሳሽ ሳሙና፣ ውሃና ሌሎች ግብዓቶች አቅርቦት ማሟላት አለመቻሉን አስረድተዋል።
ከፌዴራል መንግስት 10 ሚሊዮን ጭንብል የሚጠበቅ ቢሆንም እስካሁን አንድ ሚሊዮን 700ሺህ ብቻ መምጣቱን ጠቁመው የመጣውም ለስምንተኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች መሰራጨቱን አስረድተዋል።
ያጋጠመውን ችግር በመፍታት የመማር ማስተማሩን ስራ ለማስቀጠልም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪክ ማህበራትና ሌሎች አካላት በተቀናጀ አግባብ ትብብራቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።
በወርልድ ቪዥን የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የሰው ኃይል አስተባባሪ አቶ ጌታአለ መንጋው በበኩላቸው ያጋጠሙ የክፍል ጥበትና የግብዓት ችግሮችን ለማቃለል ከትምህርት ቢሮው ጋር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ድርጅቱ ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚያስችሉ የህክምና ቁሳቁስ፣ ሳኒታይዘርና የውሃ አቅርቦትን ለማሟላት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በቀጣይም ያጋጠመውን ችግር በመፍታት የመማር ማስተማሩን ስራ ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ድርጅቱ አስፈላጊ በጀት በመመደብ ይሰራል ብለዋል።
ስድስት የመማሪያ ክፍሎችና ሁለት መፀዳጃ ቤቶች በሰሜን ሸዋ ዞን መገንባቱን የገለፁት ደግሞ የትምህርት ለዘላቂ ልማትድርጅት የአማራ ክልል ምክትል ዳይሬክተር አቶ አዕምሮ ሙሴ ናቸው።
ከ10 ሺህ በላይ የአፍና የአፍንጫ ጭንብል ለትምህርት ቤቶች ማሰራጨታቸውን ጠቁመው በቀጣይም ክፍተቶችን በመለየት ችግሩን ለማቃለል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በምክክር መድረኩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።