ማህበሩ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሰራ ጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሰራ ጠየቀ
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እንዲደረግ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማህበር ጠየቀ ፡፡
ማህበሩ በይፋ መመስረቱ ተበስሯል፡፡
የማህበሩ መሥራችና የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ መላኩ ተክሌ ዛሬ ማህበሩ ይፋ በሆነበት መርሃ ግብር ላይ እንደተናገሩት ማህበሩ የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል ይሰራል፡፡ ፍትህ እንዲረጋገጥላቸውም ይታገላል፡፡
አካል ጉዳተኞች ሰብዓዊ መብታቸው የሚጣስበት፤ የትምህርት ተደራሽነት ውስንነት፤ የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ ታሳቢ የማያደርጉበትን ሁኔታ መቀየር እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡
በራሳቸው ተንቀሳቅሰው መስራት የማይችሉ አካል ጉዳተኞች በአገሪቱ በኢኮኖሚ ባለመደገፋቸው ለችግር የሚዳረጉበት ሁኔታ ይስተዋላል ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ችግሩ ለመንግሥት ሳይተው፤በማህበረሰብ ተሳትፎ መፈታት አለበት ብለዋል፡፡
የማህበሩ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ በበኩላቸው እየተዘጋጀ ባለው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ አካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለፕላንና ልማት ኮሚሽን እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡
ከነዚህም ፍትህን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ማድረግና የአካል ጉዳተኞች ማህበራዊ አካታችነትን ማረጋገጥ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡
ከመረጃ አያያዝ፣ ከወሊድ አመዘጋገብ፣የአካል ጉዳተኞችን ተሳታፊነት ከማጎልበት፣ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ መኖሪያ ቤቶች መገንባት በዕቅዱ ትኩረት እንዲሰጥባቸው ይጠየቃል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው "በአካል ጉዳተኞች የሚነሱትን ጥያቄዎች ለመፍታት ማነቆ የሆኑ ህግና ፖሊሲዎችን ማስተካከል ይገባል''በማለት ተናግረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ አካላት በሰጡት አስተያየት ህብረተሰቡ አካል ጉዳተኞች በተመለከተ ያለውን አመለካከት ለመቀየር እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ማህበር በህዳር 2012 በዓዋጅ ቁጥር 1113/2011 በሲቪል ማህበረሰብ ድርጀቶች ኤጀንሲ መመዝገቡን የማህበሩ መረጃ ያሳያል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትና የዓለም ባንክ ባጠኑት ጥናት በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ብዛት ከጠቅላላው ሕዝብ 17ነጥብ6 በመቶ ነው።