ጉባኤው በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ጉባኤው በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ገለጸ
ዲላ ሐምሌ 9/2010 በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለመፍታትና በዚህ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች በቂ ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ፡፡ የጉባኤው አባላት በፀጥታው ችግር ምክንያት ተፈናቅለው በጌዴኦ ዞን የሚገኙ ዜጎችን ጎብኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሀ በዚህ ወቅት እንዳሉት የጉብኝቱ አንዱ ዓላማ በችግሩ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉበትን ሁኔታ በመመልከት በጎ አድራጊ ድርጅቶች በቂ ድጋፍ እንዲሰጡ ግፊት ለማደረግ ነው፡፡ ሌላው በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ጉባኤው ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ "የኃይማኖት ተቋማት የመጀመሪያ ተልዕኳቸው ሰላምን ማስፈን ነው" ያሉት ሰብሳቢው በህዝቡ መካከል ሠላም እንዲሰፍን የማስተማርና የመቀስቀስ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህ ዓላማ ስኬታማነት የኃይማኖት ተቋማት በጋራ መሥራታቸው ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ የጉባኤው የቦርድ አባል ቄስ ደረጀ ጀንበሩ ዜጎች ተፈናቅለው የሚገኙበት ሁኔታ እንዳሳዘናቸው ገልፀው "የማይገባ በወንድማማቾች መካከል የተፈጠረ ችግር ነው" ብለዋል ፡፡ የኃይማኖት አባቶች በህዝቦች መካከል ሠላም እንዲሰፍን በግንባር ቀደምትነት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግስት ብቻውን ሁሉም ችግሮችን ይወጣል ብሎ ማሰብ ተገቢ እንዳልሆነ የጠቁሙት ቄስ ደረጀ፤ የተቋማቱ ጉባኤ አቅሙ በፈቀደ ሁሉ ተፈናቃዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ሰላም የሁሉም ኃይማኖት ተቀዳሚ አስተምህሮ በመሆኑ ሊዚህም ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ያመለከቱት ደግሞ ሌላው የጉባኤው የቦርድ አባል ፓስተር አንጋው ጌታሁን ናቸው፡፡ ግጭት ውስጥ የገቡ ህዝቦችን ከማስታረቅ ባለፈ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት በየቤተ እምነቱ ምዕመናኑን ለማስተማር ጉባኤው በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡ የኢዜአ ሪፖርተር ከነጋገራቸው ተፈናቃዮች መካከል ወጣት ካሳሁን ደገፈ በሰጠው አስተያየት የኃይማኖት አባቶች መጥተው ያሉበትን ሁኔታ በመመልከታቸው መጽናናታቸውን ተናግሯል፡፡ ዘላቂ ሰላም ተፈጥሮላቸው ወደ ነበሩበት ተመልሰው መኖር እንደሚፈልጉ ጠቅሶ፤ እየተደረገላቸው ካለው የምግብ ድጋፍ በተጨማሪ አልባሳትና ሌላም እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል፡፡ በጉብኝቱ ከሁሉም የኃይማኖት ተቋማት የተወከሉ የጉባኤው አባላት በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳና ዲላ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጎበኝተዋል፡፡