ቦርዱ የፖለቲካ ለፓርቲዎች ያዘጋጀውን ማዕከል አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
ቦርዱ የፖለቲካ ለፓርቲዎች ያዘጋጀውን ማዕከል አስረከበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ያዘጋጀውን ማዕከል ለፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ለሴት ፓርቲ አባላት ምክር ቤት አስረከበ።
ቦርዱ ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ያደረገውን የቁሳቁስ ዝግጅት ለፖለቲካ ፓርቲዎች በማስጎብኘት፣ የማዕከሉን የቢሮ ቁልፍ ርክክብ ዛሬ አካሂዷል።
ማዕከሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዳራሽ፣ የኢንተርኔትና ሌሎች አገልግሎትን የሚሰጥ ሲሆን፤ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት አቅም ግንባታ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።
ማዕከሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና በመቋቋም ላይ ላለው የሴት ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ምክር ቤት ቢሮ ማካተቱም ተገልጿል።
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ እንዳሉት ማዕከሉ በፖለቲካ ፓርዎች የጋራ ምክር ቤት የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ የተቀመጡትን ተግባራት ለማስፈጸም ያግዛል።
ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ከሴት ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ምክር ቤት ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት ለማሳለጥ እንደሚረዳውም ተናግረዋል።
እንደ ምክትል ሰብሳቢው ገለጻ ማዕከሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ከፓርቲያቸው ጋር ግንኙነት ያላቸው ሥራዎችን የሚያከናውኑበትና መረጃ የሚያገኙበት ይሆናል።
በተመሳሳይ በመቋቋም ላይ ያለው የሴት ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ምክር ቤት ከጋራ ምክር ቤቱ ጋር በቅንጅት ስራዎቻቸውን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርለት አስታውቀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም ማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ያግዘዋል ብለዋል።
የሴት ፖለቲከኞች የጋራ ምክር ቤትን ለማቋቋም በአባልነት የሚሰሩት ወይዘሮ ነቢሃ መሐመድ ማዕከሉ የሴት ፖለቲከኞችን ቁጥር ለማሳደግ ለሚያደርጉት ሥራ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።
ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ በቦርዱ እንደሚተዳደርም ተገልጿል።
በሌላ በኩል ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የተደረገው የምርጫ ቁሳቁስ ዝግጅት ግልጽና ፍትሃዊ ምርጫ ለማድረግ እንደሚያግዝ በጉብኝታቸው መታዘባቸውን የፓርቲ አመራሮች ገልጸዋል።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሐሰን ሞአሊን ቀደም ሲል ከተደረጉ ምርጫዎች የተሻለና ዘመናዊ የቁሳቁስ ዝግጅት መደረጉን እንደታዘቡ ተናግረዋል።
"የቁሳቁስ ዝግጅት ብቻውን ፍትሃዊ፣ ተአማኒና ነጻ ምርጫ ለማድረግ ማረጋገጫ ባለመሆኑ የተቋማት ገለልተኝነት ላይ መሰራት አለበት" ብለዋል።
ባለፉት 20 ዓመታት በትጥቅ ትግል ላይ የነበረው ፓርቲያቸው በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ቁሳቁስ ዝግጅቱን 90 በመቶ ማጠናቀቁን መግለጹ ይታወሳል።