ቀጥታ፡

ብክለትን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ አገልግሎት ላይ ዋለ

አዳማ ጥቅምት 13/2013(ኢዜአ) የልማት ፕሮጄክቶችና አምራች ተቋማት በአካባቢው ላይ የሚያስከትሉትን ብክለት አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ አገልግሎት ላይ ማዋሉን የደን አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ የአየር፣ ውሃ፣ አፈርና ድምፅ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂዎችን ዛሬ በአዳማ ከተማ ለሁሉም ክልሎች አስረክበዋል።

የደን አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በዚህ ወቅት እንዳሉት የልማት ፕሮጀክቶችና አምራች ተቋማት በአካባቢ  ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ብክለት አስቀድሞ  ለመከላከልና ለመቀነስ ቴክኖሎጂው የላቀ ሚና አለው።

የአካባቢ ግምገማ ጥናትና ዕቅድ ሳይኖራቸው ማንኛውም ዓይነት ፕሮጀክት ወደ ስራ እንደማይገባ ተናግረዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ አገልግሎት ላይ የዋሉት ቴክኖሎጂው የአየር፣ውሃ፣ አፈርና ድምፅ ብክለትን ለመለካትና ለመቆጣጠር ብሎም አካባቢያዊና ሰነ ምህዳራዊ ህይወት ለመጠበቅ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት ከ19ሺህ በላይ የብክለትና ብክነት ችግር ያለባቸው ፕሮጀክቶች ላይ በተለያዩ ቦታዎች የተፅዕኖ ግምገማ መድረጉን ጠቅሰዋል።

በዚህም አብዛኞቹ የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጅ እንዲገነቡ መደረጉን ተነግሯል።

በሁሉም የልማት ፕሮጀክቶችና አምራች ተቋማት የአካባቢ ኦዲት፣ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ኢንዲዘረጉ ተደርጓል ነው ያሉት።

አሁን ለክልሎች የተሰጠው ቴክኖሎጂ ብክለት ለማወቅና ጉዳት እንዳይደርስ ቀድሞ ለመከላከል ሚናው የላቀ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ክልሉ ትላልቅ የኢንቨስትመንት ተቋማት ስለሚኖሩበት ለብክለት የተጋለጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰይፈዲን መሐዲ ናቸው።

በተለይ አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የክልሉ ዞኖች የአየር፣ውሃ፣ አፈርና የድምፅ ብክለት ችግር አለባቸው ብለዋል።

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ስራ ላይ ያሉትም ሆኑ አዳዲስ ወደ ስራ የሚገቡ የልማት ፕሮጀክትና አምራች ተቋማት የአካባቢያዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናትና ዕቅድ ሳያቀርቡ ወደ ስራ እንዳይገቡ መደረጉን አመላክተዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት ሁሉም የልማትና ኢንቨስትመንት ተቋማት እንዲተገብሩ ለማስቻል ግብ አስቀምጠን እየሰራን ነው ብለዋል።

የውሃና የአፈር ብክለት ናሙና ጥናትና ምርምር ላቦራቶሪ በክልሉ መቋቋሙን ያመለከቱት አቶ ሰይፈዲን በውሃ ብቻ ላይ የነበረው የብክለት መጠን ልኬት ዘንድሮ በአየር፣አፈርና ድምፅም ላይ ልኬት እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

 በዚህም ከ500 ፕሮጀክትና የኢንቨስትመንት ተቋማት ናሙና መወሰዱን ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ በበኩላቸው ከዚህን በፊት ብክለትን ለመለካት የዓይን ዕይታ ብቻ ነበር የሚንጠቀመው በዚህም የብክለት ደረጃና የጉዳት መጠን ማወቅ አንችልም ነበር ብለዋል።

በተለይ በጣና ሐይቅ ዙሪያ በርካታ የልማት ፕሮጀክትና የኢንቨስትመንት ተቋማት እየተስፋፋ በመሆኑ  የብክለት መለኪያ ቴክኖሎጂው አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ጣና ሐይቅ በእንቦጭ አረም የተወረረው ቀደም ሲል ውሃው ከተለያዩ ተቋማትና አካባቢ በሚወጣ ቆሻሻና  በመበከሉ ነው ብለዋል።

አሁን በውሃ፣ አፈር፣ አየርና ድምፅ የሚኖረውን ብክለት ለመለየትና ጉዳቱን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ከኮሚሽኑ በማግኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አሁን ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅሰቃሴዎችን ከአካባቢ ደህንነት ጋር ለማጣጣም የሚረዳ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም