የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ደም ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ደም ለገሱ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ዛሬ ደም ለግሰዋል።
ሠራተኞቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም ባንክ ባቀረበው ጥሪ መሰረት ነው ልገሳውን ያደረጉት።
ደም መለገስ የወገንን ሕይወት መታደግ መሆኑን የገለጹት ሠራተኞቹ ኅብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን በማዳበር ለወገኑ አለኝታነቱን በተግባር እንዲያሳይ ጠይቀዋል።
ጋዜጠኞቹ እንደገለጹት ከለጋሾች የሚገኘው ደም በተለያዩ ምክንያቶች የጤና እክል ለሚያጋጥማቸው ወገኖች የሚውል በመሆኑ ደም ልገሳ የሁልጊዜ ተግባር ሊሆን ይገባል ።
አቶ አወድ አብዱልሰቡር አንድ ሰው ደም ሲሰጥ የሶስት ሰዎች ህይወትን መታደግ እንደሚችል ተገንዝቦ ደም መስጠትን ባህል ቢያደርግ መልካም ነው በማለት ተናግረዋል።
አቶ ጌታሁን ዳዲ በበኩላቸው ሁሉም ሰው ደም ቢሰጥ በተለይ በአደጋ ጊዜ ለሚጎዱ ወገኖች ፈጥነን ለመድረስ እንችላለን ብለዋል።
ደም መስጠት ማለት ህይወት መስጠት ማለት መሆኑንና በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ደም በመስጠት የብዙ ወገኖችን ህይወት መታደግ እንደሚቻል የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ የሺመቤት ደመቀ ናቸው።
የብሔራዊ ደም ባንክ ተወካይ ሲስተር ኤሚሊያ ኃይሌ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየው የደም ልገሳ አሁን ላይ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
አቅም በሚፈቅደው ልክ ሰዎችን ለመርዳት ከሚደረጉ በጎ ተግባራት አንዱ ደም መለገስ በመሆኑ ይህንን ባህልና ልምድ በማድረግ በየሶስት ወሩ ደም በመለገስ የሌሎች ሕይወትን መታደግ ያስፈልጋል ብለዋል።