በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለህዳሴ ግድብ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለህዳሴ ግድብ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13/2013 (ኢዜአ) በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በጽህፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ዜጎች ለግድቡ የሚያደርጉት ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በተለይም ከውሃ ሙሌቱ ጋር ተያይዞ የህዝቡ ተነሳሽነትና ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ነው ያሉት።
በዚህም በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም ብቻ 109 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ያስታውሳሉ።
እንዲሁም ነሐሴ ወር ላይ ከ152 ሚሊዮን በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን በመስከረም ወር ላይ ደግሞ 197 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
በመስከረም 2013 ዓ.ም የተገኘው 197 ሚሊዮን ብር ገቢ እስከዛሬ ለግድቡ ግንባታ በወር ከተሰበሰበው ገቢ ከፍተኛው መሆኑን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በመጀመሪያው በሩብ ዓመት 507 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን አቶ ኃይሉ ጠቁመዋል።
ይህም ኢትዮጵያዊያን የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የህዝቦች ህልውና እና የሉአላዊነት ጉዳይ መሆኑን በተግባር ያሳዩበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለግድቡ ግንባታ በአጠቃላይ 160 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስም በአጠቃላይ ለግድቡ ግንባታ 121 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ከዚህ በኋላ ለሚኖረው ስራም 40 ቢሊዮን የሚሆን ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ይህንንም ህዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል የግድቡ ግንባታ እስከሚ ጠናቀቅ ድረስ ያሳየውን ድጋፍና ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የግድቡ የግንባታ ሂደት 76 በመቶ መድረሱን ወቅታዊ መረጃዎች ያሳያሉ።