ዶናልድ ትራምፕና ቭላድሚር ፑቲን በሄልሲንኪ  ፊት ለፊት ተገናኝተው ተወያዩ

16
ሐምሌ 9/2010 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሩስያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ዛሬ በፊንላንድ ዋና ከተማ ሄልሲንኪ ለውይይት ፊት ለፊት ተገናኝተዋል። ሁለቱ መሪዎች ከዚህ ቀደም ከራሳቸው ሀገር ውጭ በገለልተኛ ሀገር ለመገናኘት ባቀዱት መሰረት ነው ዛሬ ሄልሲንኪ የከተሙት፡፡ በሀገሮቻቸው የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ በይፋዊ የትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ አሜሪካ ከዚህ ቀደም በነበሩት መሪዎቿ አማካይነት ታራምደው የነበረውን ሩሲያን በጥርጣሬ የመመልከትና የማግለል አካሄድ ተችተዋል፡፡ አሜሪካ ከዚህ ቀደም በሩሲያ ላይ የነበራት አተያይ የሞኝና ማስተዋል ያልታከለበት ነበር ነው ያሉት። የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በትራምፕ አስተያየት “አዎ እንስማማለን” የሚል መልስ ሰጥቷል። አሜሪካ ከዚህ ቀደም ሩስያ ክሬሚያን ከዩክሬን ገንጥላ ወስዳለች በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ያሰማች ሲሆን ማዕቀብ ስታዝጎደጉድ መኖሯም ይታወቃል። የትራምፕ ሰሞናዊ አስተያየት ግን በዋይት ሀውስ አዲስ የውይይት አጀንዳን የሚከፍት ነው እየተባለ ይገኛል። በ2016 የአሜሪካ ምርጫ ላይ ሩስያ ጣልቃ ገብታለች የሚሉ ድምፆች መበርከታቸው የሚታወስ ሲሆን ይህን የሚያጣራ ኮሚቴም ተዋቅሮ ስራ መጀመሩ ይታወቃል። ሌላው የአሜሪካና የሩስያ አለመግባባት መነሻ ደግሞ ሩስያ በሶሪያ የበሽር አል አሳድ መንግስትን በጦር እያገዘች ነው የሚል መከራከሪያ ነው። ለመሆኑ ሁለቱ መሪዎች ሄልሲኒኪን ለመገናኛ ለምን መረጧት ሄልሲንኪ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በፖለቲካዊና ወታደራወ ጉዳዮች ገለልተኛ  መዲና ሆና መገኘቷ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። የቀድሞዋን ሶቪየት ህብረትና ምዕራባውያን ሀገራትን ግንኙነት የተሻለ ለማድረግ በፈረንጆቹ 1975 ሄልሲንኪ ላይ ስምምነት መፈረሙም ሌላው መነሻቸው ነው። ሄልሲንኪ ከቀድሞዋ ሲቪየት ህብረት በኋላም የሩስያና የአሜሪካ መሪዎች መገናኛ ማዕከል ናት። ትራምፕና ፑቲን በሄልሲንኪ ተገናኝተው ሲወያዩ ከሶቪየት ዘመን በኋላ አራተኛው የሀገራቱ መሪዎች ጉባኤ ሆኗል። ምንጭ፦ቢቢሲና ሬውተርስ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም