ቀጥታ፡

ኮሮናቫይረስና መሰል አገራዊ ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙት መማር እና መመራመር በሚችል ትውልድ ነው... ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2013( ኢዜአ) ''ኮሮናቫይረስና መሰል አገራዊ ችግሮችን የሚያጠፋ ትውልድ ማግኘት የሚቻለው በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጭምር መማር እና መመራመር የሚችል ትውልድ በመፍጠር ነው'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መጀመርን አስመልክተው ከአፀደ ህጻናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላሉ ተማሪዎች ዛሬ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ መንግስት በቀዳሚነት የወሰነው ውሳኔ ''የእናንተን የነገ አገር ተረካቢዎቻችን ህይወት መታደግ ነበር'' ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው።

በዚህም ትምህርት ቤቶችን በፍጥነት በመዝጋትና ሌሎች የመከላከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ስጋትና አደጋ በእጅጉ መቀነስ መቻሉን ነው ያነሱት።

ትምህርት ቤቶችም በፍጥነት እንዲዘጉ የተደረገበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ "ቫይረሱ አገር ውስጥ በተከሰተበት ጊዜ የመከላከል፣ የመመርመርና የማከም አቅማችን እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነበር" ብለዋል።

''ቫይረሱ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዴት መቋቋም እንደምንችል በቂ ልምድ አልነበረንም፤ በዚህ ምክንያት በልጆቻችን ላይ አንዳች ቸልታ ማሳየት ተገቢ እንዳልሆነ መግባባት ላይ ደርሰን ነበር፤ ለዚህ ነበር ትምህርት ቤቶችን የዘጋነው''ብለዋል።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገኘ ሰባት ወራት ያለፈው መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በአሁኑ ወቅት የሕክምና ባለሙያዎችና የጤና ተቋማት ስለጉዳዩ የተሻለ ሙያዊ ብቃት ማዳበራቸውን ነው ያመለከቱት።

ከዚህ ባለፈ የመመርመር አቅም ማደጉንና የህብረተሰቡም ስለበሽታውና ስለመከላከያ ዘዴው በቂ ግንዛቤ ከማግኘት ባለፈ የመከላከያ ቁሶችን በቀላሉ በቤት ውስጥ መስራት መቻሉን አስረድተዋል።

"ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ከዚህ ጊዜ በላይ ትምህርት ቤቶቻችንን ዘግቶ ማቆየት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

''ዓለም ራሷን ከኮሮናቫይረስ እየተከላከለች እንቅስቃሴዋን መቀጠል የግድ ሆኖባታል፤ እኛም በአንድ በኩል እየተጠነቀቅን በሌላ በኩል ደግሞ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎቻችንን ማከናወን እንዳለብን እናምናለን'' ብለዋል።

''ኮሮናን እና መሰል አገራዊ ችግሮችን የሚያጠፋ ትውልድ ማግኘት የሚቻለውም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጭምር መማር እና መመራመር የሚችል ትውልድ በመፍጠር ነው'' ሲሉም ዶክተር ዐቢይ በመልዕክታቸው አብራርተዋል።

ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ውጤታማ ሆነው ለክብር የደረሱት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፈው መሆኑን አስታውሰው፤ ሳይንቲስቶች፣ ምሁራንና ሊቃውንት ለማዕረግ የበቁት በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ተምረው መሆኑን አመልክተዋል።

"ጀግና የሚፈጠረው በችግር ጊዜ በመሆኑ የኮሮና ወቅት የብዙ ጀግና ተማሪዎች መፍጠሪያ ጊዜ ይሆናል" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስተሩ አክለዋል።

ከተማሪዎች ባለፈ ወላጆች፣ መምህራን፣ የትምህርት ቤት አስተዳደር ሰዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና የጸጥታ አካላት ኮሮናን በትምህርት የሚያሸንፍ ትውልድ እንዲፈጠር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ዶክተር ዐቢይ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም