አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአንድ ጸረ-ቫይረስ መድሃኒት ሙሉ እውቅና ሰጠች

68

በአሜሪካ ጸረ-ቫይረስ ለሆነው ሬምዲሲቪር የተሰኘ መድሃኒት በሆስፒታሎች ህክምና ላይ ለሚገኙ የኮቪድ -19 በሽታ ህሙማን እንዲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ እውቅና መሰጠቱ ተገለጸ።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ የብራንድ ስሙ ቬክሉሪ የተሰኘው መድሃኒት ከቫይረሱ ለማገገም የሚወስደውን ቀናት በአማካኝ በ5 ቀናት እንደሚቀንስ በክሊኒካዊ ሙከራ መረጋገጡን የአሜሪካ የምግብና መድሃኒት አስተዳደር አስታውቋል።

በሌላ በኩል የአለም የጤና ድርጅት ባካሄደው ጥናት መድሃኒቱ በኮቪድ -19 በሽታ ለተያዙ ህሙማን በህይወት የማቆየት ጠቀሜታው አነስተኛ አሊያም ምንም አስተዋጽኦ የሌለው መሆኑን ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ በዘገባው ተጠቅሷል።

የመድሃኒቱ አምራችም የድርጅቱን የጥናት ግኝቶች መቃወሙ ተገልጿል።

በአሜሪካ መድሃኒቱ ከግንቦት ወር ጀምሮ ለድንገተኛ የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ እንደሆነም ተመልክቷል።

በቅርቡም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮና ቫይረስ በተገኘባቸው ወቅት መድሃኒቱ ተሰጥቷቸው ከበሽታው ማገገማቸው በዘገባው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም