በምስራቁ ክፍል አብዛኛው አካባቢዎች ላይ የተከሰተ አንበጣ መንጋን መቆጣጠር ተቻለ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቁ ክፍል አብዛኛው አካባቢዎች ላይ የተከሰተ አንበጣ መንጋን መቆጣጠር ተቻለ
ድሬዳዋ፣ ጥቅምት 13 (ኢዜአ) ከሶማሌ ክልል በቀር በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል አብዛኛው አካባቢዎች የተከሰተ የአንበጣ መንጋን መቆጣጠር መቻሉን የተጎራባች ክልሎች የአንበጣ መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የሚመራ የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች የአንበጣ መከላከል ግብረ ኃይል መግለጫ ሰጥቷል።
ግብረ ኃይሉ እንዳስታወቀው በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች ፣ በሐረሪና በድሬዳዋ አብዛኛው አካባቢዎች የተከሰተ አንበጣ መንጋን መቆጣጠር ተችሏል።
አንበጣ መንጋው በመኽር ሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬና በግጦሽ ሳር ላይ ጉዳት ቢያደርስም በአውሮፕላን በመታገዝ በተካሄደ የመከላከል ስራ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተመልክቷል፡፡
የግብረ ኃይሉ አባልና የኦሮሚያ ክልል የግብርና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንዳስታወቁት የአንበጣ መንጋውን ለመቆጣጠር አርሶና አርብቶ አደሩን እንዲሁም የጸጥታ አካሉን ያሳተፈ ያላሰለሰ ጥረት ተደርጓል።
በምስራቅ ሐረርጌ ከደደር ወረዳ በስተቀር የአንበጣ መንጋው የሚያድርበት ስፍራ ሙሉ ለሙሉ ነጻ መደረጉን ተናግረዋል።
የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በማስፋት ወደ ሶማሌ ክልል እየገባ ያለውን የአንበጣ መንጋ የመከላከል ዘመቻ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚካሄድ አመለላክተዋል።
ለአንበጣ መከላከል ወደ ሀገር ውሰጥ የገቡ አውሮፕላኖች በቀጠናው መንጋውን ለመቆጣጠር የላቀ አስተዋጻ ማድረጋቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል።
የግብረ ኃይሉ አባልና የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው በአንበጣው የወደመውን የመኽር እርሻ ፈጥነው በሚደርሱ ዘር ለመተካት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ግብርና ሚኒስቴርና ክልሎች ውሃ ገብ ለሆኑ አካባቢዎች በቶሎ የሚደርሱ ምርጥ ዘሮችን ለማሰራጨት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልፀዋል፡፡
በድሬዳዋ አስተዳደር የአንበጣ መንጋ ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን የገለጹት ኃላፊው "በድንገት ሊመጣ የሚችልን መንጋ በፍጥነት ለመከላከል ሁሉም በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል" ብለዋል፡፡
የአንበጣ መንጋው በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ያደረሰው ጥፋት እየተጠና መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል ።