መሻሻል ባለባቸው ህጎች ላይ ጥናት እንዲያቀርብ የተቋቋመው አማካሪ ካውንስል በድርድሩ ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር የፖለቲካ ፓርቲዎች አሳሰቡ

71
አዲስ አበባ ሐምሌ 9/2010 በኢትዮጵያ መሻሻል ባለባቸው ህጎች ላይ ጥናት እንዲያቀርብ በመንግስት የተቋቋመው አማካሪ ካውንስል በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሳሰቡ። ለ3 ወራት ተቋርጦ የነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር 11ዱ ተደራዳሪ ፓርቲዎች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ድርደሩ ዛሬ ተጀምሯል። ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ ውይይቱ የተቋረጠበትን ምክንያት ለገዢው ፓርቲ አቅርበው ውይይት ተደርጓል። በሀገሪቱ አልፎ አልፎ በተከሰተው የሰላም መጓደል አመራሩ ዜጎችን ለማረጋጋት የስራ ጫና ውስጥ መክረሙ ለድርድሩ መቋረጥ የመጀመሪያው ምክንያት እንደሆነ  የኢህአዴግ ተደራዳሪ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በውይይቱ መክፈቻ ላይ አስረድተዋል። በተጨማሪም በብሄራዊ መግባባት ላይ የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳብ በጊዜ አለመድረሱም ለድርድሩ መቋረጥ ሌላኛው ምክንያት ነው ብለዋል። አሁን ላይ የሁሉም ሃሳብ መጥቶ የተደራጀ መሆኑን የገለፁት አቶ ፍቃዱ በምን አግባብ እንደራደር በሚለው ሃሳብ ላይ ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት እየተደረገበት ነው ብለዋል። በማስከተል በፓርቲዎቹ ለድርድር የቀረቡ የፀረ ሽብር ህግ፣ የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ፣ የፕሬስ አዋጅ፣ የዲሞክራሲ ተቋማት አሰራርና አደረጃጀት የሚመለከት ህግ፣ የምርጫ ቦርድ፣ የፍትህ ስርዓት ማሻሸያ፣ የንግድና የወንጀል ህጎችን ከመንግስት ውጭ የሆኑ ምሁራን ሳይንሳዊ ጥናት እንዲያደርጉ ምሁራንን ያካተተ የአማካሪ ምክር ቤት መቋቋሙን አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል። ሆኖም አማካሪ ካውንስሉ የሚያጠናው በድርድር አጀንዳዎች ላይ መሆኑ በድርድሩ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ተደራዳሪዎች ያነሳሉ። ከ11ዱ ተደራዳሪ ፓርቲዎች ዶክተር ጫኔ ከበደ እንደተናገሩት  የተቋቋመው አማካሪ ካውንስል ስራውን እንዲቀጥል መደረጉ “ያለውይይትና  ድርድር በፓርላማ የሚጸድቅ ረቂቅ ይዞ ይመጣል” የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡ አቶ ገብሩ በርሄ ከኢዴህ ፓርቲ “የኛ አጀንዳ ለሌሎች ባለሙያዎች መሰጠቱ ከፈረሱ ጋሪው የቀደመ ይመስለኛል ፤ መጀመሪያ የሁለታችንን ግብዓት ማግኘት አለበት''  ብለዋል፡፡ አቶ ፍቃዱ በበኩላቸው የአማካሪ ካውንስሉ ያጠናው ነገር ለድርድር ይቀርባል እንጅ በቀጥታ አይፀድቅም ብለዋል። ካውንስሉ ለድርድሩ የሚሆኑ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከሀገሪቱ እውነታ ጋር እያዛመዱ ሃሳቦችን ያቀርባሉ ድርድርም ይደረግበታል ብለዋል። ግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ.ም በምርጫ ቦርድ እውቅናን ያገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ኮንግረስ ፓርቲ ድርድሩ ባለበት ተካፋይ ሆኖ እንዲገባ ወስነዋል። የፓርቲው አባላት በሰላማዊ ትግልና በድርድር ስለምናምን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመታገልና ለሀገር ይጠቅማሉ ያልናቸውን ሀሳቦች ለማቅረብ መጥተናል ብለዋል። ድርድሩን ለመቀጠል በቀጣይ ሳምንት ሀሙስ ቀጠሮ ተይዟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም