"የአገር መከላከያ ሠራዊቱ ከፖለቲካው ጋር የሚወድቅ የሚነሳ ሳይሆን ከአገርና ከሕዝብ ጋር የሚዘልቅ ነው"... ሜጀር ጀኔራል ሹማ አብደታ - ኢዜአ አማርኛ
"የአገር መከላከያ ሠራዊቱ ከፖለቲካው ጋር የሚወድቅ የሚነሳ ሳይሆን ከአገርና ከሕዝብ ጋር የሚዘልቅ ነው"... ሜጀር ጀኔራል ሹማ አብደታ
አዲስ አበባ ጥቅምት 12/2013 (ኢዜአ) "እየተገነባ ያለው የአገር መከላከያ ሠራዊት ከፖለቲካው ጋር የሚወድቅ የሚነሳ ሳይሆን ከአገርና ከሕዝብ ጋር ዘላቂነት ያለው ነው" ሲሉ በሠራዊቱ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ሹማ አብደታ ተናገሩ።
ሜጄር ጄኔራሉ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ ሠራዊቱ በሰው ኃይል ስብጥርና በአመራር አደረጃጀቱ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰዋል።
በተለይ ከብሄር ብሄረሰቦች ተውጣጥቶ ኢትዮጵያን የሚወክል እንዲሆን የተደረገው ስራ ትልቅ ውጤት የታየበት እንደሆነም ገልፀዋል።
ከቁጥር አንፃር ሚዛናዊ የሆነ ስራ መስራትና ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የሚወክል በማድረግ ረገድ ጠንካራ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
እንደ ሜጀር ጄኔራል ሹማ ገለጻ ሠራዊቱ ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት ነፃ ሆኖ አገራዊ ተልዕኮውን የሚወጣበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ሠራዊቱን በአዲስ መልክ ከማጠናከር ስራው ጋር ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የአመለካከት ለውጥ ማምጣት፣ አደረጃጀቱን ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ፣ ደረጃውን የጠበቀ የተግባር ስልጠናና ብቃት ማሟላትና ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ ልክ ትጥቅ እንዲኖረው ማድረግን ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ ሠራዊቱ የአገር ሉዓላዊነት፣ ሠላምና መረጋጋትን ማስጠበቅ በሚችልበት ደረጃ ላይ መሆኑን ሜጀር ጄኔራሉ ተናግረዋል።
የአሸባሪነት ተግባር በዓለም መስፋፋት ዋነኛ የሠላም እጦት ምክንያት እየሆነ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በስልጠናዎች የዳበረና ብቃት ያለው ሠራዊት የመገንባት ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏልም ብለዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ አዲስ ካቋቋመችው የባሕር ኃይል ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ ኃይል መዘጋጀቱን ነው የገለፁት።
ይህ ደግሞ ሽብርን ከመከላከል አንፃር እንደ አገር የነበረውን ተሳትፎና ብቃት ከፍ ለማድረግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ሠራዊቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በከተሞችና በአስቸጋሪ ተልዕኮዎች ላይ ግዳጅ መወጣት የሚያስችል ብቃት እንዲኖረው እየተደረገ እንደሆነም አንስተዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ብላቴ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን የሠራዊት አባላት ከነገ በስቲያ እንደሚያስመርቅም ሜጀር ጄኔራል ሹማ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ተመራቂዎቹ መከላከያ ሠራዊቱ ለአገር ሉዓላዊነት መከበርና ለሠላም እየሰራ ያለውን ስራ የማጠናከር ድርሻ እንዳላቸውም ገልፀዋል።