ከጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ባለፉት ሶስት ወራት 40 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ከጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ባለፉት ሶስት ወራት 40 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12/2013(ኢዜአ) ከጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ባለፉት ሶስት ወራት 40 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለፀ።
የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የ2013 በጀት አመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የአፈፃፀምና የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ዙሪያ ከተቋሙ ስራተኞች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱም የሩብ አመት አፈፃፀም፣ የዘርፉ ነባራዊ ሁኔታ፣ የ10 አመት መሪ ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫ ተዳሷል።
የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ፤ ባለፉት ሶስት ወራት ከዘርፉ 40 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን ገልጸዋል።
በዓለም ለተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽን የደህንነት መከላከያ አልባሳት ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ እንደነበረም ተናግረዋል።
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የተቀዛቀዙ ፋብሪካዎችን ወደ ስራ መመለስ፣ ከገዥዎች ጋር ማገናኘት እና የውጭ ንግዱን ማስቀጠል በዕቅዱ መካተታቸውን ገልፀዋል።
ፋብሪካዎችን የማማከር እና የመደገፍ ስራ መስራቱንም አቶ ስለሺ ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ የአገሪቱን የ10 አመት መሪ የልማት ዕቅድ ባገናዘበ መልኩ ዕቅድ ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
ዕቅዱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለኢንዱስትሪ የሚሆን ግባዓት በሀገር ውስጥ ማምረትና የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት እንዳደረገ አመላክተዋል።
ለዘርፉ የሚያስፍልጉ ግብዓት ከማሟላት አንፃር በ2022 ዓ.ም የጥጥ የመሬት ሽፋን ከነበረበት 55 ሄክታር ወደ 411 በማሳደግ 2 ነጥብ 35 ቶን ጥጥ ለማምረት መታቀዱን ገልፀዋል።
የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት፣ የምርት ጥራታቸውን በማስጠበቅና የገብያ ተደራሽነትን ለማስፋፋት መታቀዱንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በ2022 ዓ.ም ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ወደ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ መታቀዱንም ገልጸዋል።
በጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ የሚፈጠረውን የስራ ዕድል ወደ 345 ሺህ ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የወጭ ንግድ ገቢ፣ የምርት ዋጋ ማሳደግ የፋብሪካዎችን ማሳደግ ኢንቨስትመንቱን ማስፋፋት ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የሙቀት አማቂ ጋዞችን ቅነሳ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ እንደነበር ተገልጿል።