ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ዝግጅት እያደረገች ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ዝግጅት እያደረገች መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪና የዓለም የንግድ ድርጅት የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ ማሞ ምህረቱ ተናገሩ።

ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት "ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከአስራ ስድስት አመት በፊት የጀመረችው ድርድር አሁን ላይ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል"።

ከዓለም ንግድ ድርጅት አባል አገራት ጋር ባለፈው ጥር ወር በተደረገው ምክክር የንግድና የኢንቨስትመንት ስርዓቱን ከአለም የንግድ ድርጅት ስምምነቶችና መስፈርቶች አንጻር መፈተሹንም ገልጸዋል።

የአገሪቱ የንግድ ሥርዓት በአብዛኛው ከዓለም የንግድ ድርጅት ሕግና ደንብ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ገልጸው የብዙ ወገን ንግድ ስርዓት አካል እንዳትሆን ወደ ኋላ የሚመልሳት ምንም ነገር የለም ብለዋል።

በተመሳሳይ ባለፈው ጥር ወር በጄኔቫ ከ8 አባል አገራት ጋር በተደረገው የሁለትዮሽ የንግድ ድርድር ወቅትም ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል ነው ያሉት።

ወደ ሁለትዮሽ ድርድር ሲመጣ ዋናው ጉዳይ በንግድ ሸቀጦች ላይ የሚጣለው ታሪፍ እና ለውጭ ባለሃብቶች የሚከፈተው የኢንቨስትመንት ወይም የአገልግሎት ዘርፍ ነው።

በመሆኑም ከአለም የንግድ ድርጅት አባል አገራት ኢትዮጵያ ቅድመ ሁኔታዎችን አጠናቃ ወደ ንግድ ድርጅቱ አባልነት እንድትቀላቀል አዎንታዊ ምላሽ መኖሩንም አስረድተዋል።

የብዙ ወገን የንግድ ስርዓት አካል መሆን መንግስት በአሁኑ ወቅት እያከናወነ የሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውጤት መሆኑንም አብራርተዋል።

የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን የመቀላቀል ሂደት ማጠናቀቁ ለኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች እና ባለሃብቶች ግልጽ እና ሊተነበይ የሚችል የውጭ ገበያ ተደራሽነትን ይፈጥራልም ነው ያሉት።

እንደ ከፍተኛ አማካሪው ገለጻ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ታሪፍ በማጥፋት ላይ ሳይሆን በታሪፍ ላይ የታሪፍ ጣራን ያስቀምጣል።

በተለይ በድርድር ወቅት አገሪቱ የምትጠቀምበት ወሳኙ የድርድር ነጥብ ኢትዮጵያ እንድ ቴሌኮም እና የፋይናንስ ተቋማት ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ለማድረግ መዘጋጀቷን ወደ አለም የንግድ ድርጅት አባልነት ለመቀላቀል እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅማበታለች ብለዋል።

መንግስት በአሁኑ ወቅት የንግድ ማሻሻያውን በማፋጠን ኢትዮጵያ የአለም የንግድ ድርጅት አባል ከመሆኗ አስቀድማ የተለያዩ የውጭ ባለሀብቶችን ወደ ቴሌኮም ዘርፉ እያስገባ ነው ብለዋል።

ዋናው አሳሳቢው ጉዳይ የፋይናንስ ዘርፉ ነው ያሉት አቶ ማሞ፤ አብዛኛዎቹ አባል አገራት ኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓቷን ስትከፍት ማየት ይፈልጋሉ ብለዋል።

በዚህ ረገድም መንግስት በኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የአለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የሚቀይረው ሲሆን፤ የንግድ ህጎችንና ስርአቱን በማዘመን ከፍተኛ የውጭ ንግድ መሳብ ያስችላታል።

በአሁኑ ጊዜ 164 የዓለም አገሮች የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ሲሆኑ፤ 24 ተጨማሪ አገራት ደግሞ ወደ ድርጀቱ ለመቀላቀል በድርድር ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም