በኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል...ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል...ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 12/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው ተናገሩ።
ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ ከፍተኛ የፖሊስ ሃላፊዎች በሰንዳፋ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስልጠና መስጠት ተጀምሯዋል።
የፖሊስ አባላቱ ስልጠና የፖሊስ ዶክትሪን፣የፖሊስ ስታንደርድ፣ የሰራዊት የለውጥ አመራርና የፖሊስ ስብዕና ግንባታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ታውቋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው በመክፈቻው ላይ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ለሀገርና ህዝብ ደህንነት የሚሰራ የፖሊስ ሃይል ማደራጀት ያስፈልጋል።
በሙያው ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራትና ዘመን ተሻጋሪ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።
ለዚሀም የፖሊስ ተቋማት የራሳቸው የሆነና የሚመሩበት ስርአት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት አመታት በፖሊስ ተቋማት ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ተቋማት ተቀናጅተው በመስራት ህዝብን ማገልግልና ህገ-መንግስቱን የማስከበር ስራቸውን እንደሚያጠናክሩም ኮሚሽነር ጀነራሉ አረጋግጠዋል።
የአሁኑ የፖሊስ ሃላፊዎች ስልጠናም የፖሊስ ዶክትሪን፣ የፖሊስ ስታንደርድ፣ የሰራዊት የለውጥ አመራር የመፍጠርና የፖሊስ ስብዕና ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ፤ ስልጠናው የፖሊስ አባላት ተመሳሳይ ተልዕኮ ኖሯቸው ስራቸውን ለመከወን እንዲችሉ ያግዛል ብለዋል።
በዩኒቨርስቲው ኮሮናቫይረስን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም በኮሚሽነሮቹ ተጎብኝተዋል።