የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ያገኛቸውን የተሻሻሉ የግብርና ምርት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ያገኛቸውን የተሻሻሉ የግብርና ምርት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 12/2013 (ኢዜአ) - የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ያገኛቸውን የተሻሻሉ የግብርና ምርት ዝርያዎችን ለአካባቢው አረሶ አደሮች በማበርከት ምርታማ እንዲሆኑ እያስቻለ መሆኑን ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው በተለይ በጤፍና የስንዴ ሰብል ዝርያዎች ላይ ውጤታማ ምርምሮችን እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሣይንስና ግብርና ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሙላቱ ካሣዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የአካባቢው አርሶ አደሮች ምርታማ እንዲሆኑ የተቻለውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
በአካባቢው በስፋት የሚመረቱ የጤፍና ስንዴ ሰብሎች ምርትና ምርታማነትን በምርምር በማሳደግ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ከሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ የጤፍ ዝርያዎችን የተለያዩ ሥነ ምኅዳር ካላቸው ወረዳዎች ወስዶ ምርምር ሲያደርግ መቆየቱንም ተናግረዋል።
በተመሣሣይ በዳቦና በማካሮኒ የስንዴ ምርት የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማውጣት ለአርሶ አደሩ ለማሠራጨት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ምርምር የሚደርግባቸው ዝርያዎች ሲወጡ ለአርሶ አደሩ በማላመድ ወደ ምርት ሂደት እንዲገቡ ዩኒቨርሲቲው እየሠራ መሆኑንም ዶክተር ሙላቱ ተናግረዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ አቅራቢያ በ50 ሄክታር መሬት ላይ የሠርቶ ማሣያና ምርምር ቦታ በማቋቋም የምርምር ሥራዎች በማከናወን እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በሰብል ምርምር ላይ በተለይም በምግብ ሰብሎች ላይ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተማረና ብቁ የሰው ኃይል ከማፍራት በተጨማሪ የጥናትና ምርምር፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራና ሽግግርን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።
በጥናትና ምርምር ሥራቸው የማኅበረሰቡን ተጠቀሚነት ማሳደግም ዋነኛ ትኩረታቸው መሆን እንዳለበት ይታወቃል።