ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ ሴት አካል ጉዳተኞች አንደበት

አዲስ አበባ ሀምሌ 9/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከበዓለ ሲመታቸው ጀምሮ የሚያሰሟቸው ንግግሮች ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ያማከሉ እንደሆኑ ብዙዎች አስተያየት ሰጭዎቹ ይገልጻሉ። ታዋቂዋ የአካል ጉዳተኞችና ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ ብዙ ጊዜ የሚደረጉ ንግግሮች በመርህ ላይ እንጂ በግል ሕይወት ላይ የተመሰረቱ አለመሆኑን ይገልጻሉ። "የዶክተር አብይ ንግግሮች ግን ይህን ልምድ የሰበሩ ናቸው" ያሉት ወይዘሮ የትነበርሽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለንግግር ማሳመሪያ ሳይሆን የሕይወታቸውን ዕውነታ የሚገለጹ እንደሆኑ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሪት ቃልኪዳን ሽመልስ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች ለችግር ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሳይቀር ሁሉንም ወገኖች ያካተቱ መሆናቸውን ያክላሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር እሳቤዎችን ወደ ሕይወታችን በመተርጎም፣ የምናልማትን ገናና አገር ዕውን ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንደሆነም ይገልጻሉ ወይዘሮ የትነበርሽ። በተመሳሳይ ወይዘሪት ቃልኪዳን 'የእንደመር እሳቤ' ሁሉንም የሚያግባባ ብቻ ሳይሆን የወደፊት ጉዟችን ስንቅ ነውና መደመር ያስፈልጋል ነው የሚሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም