ቀጥታ፡

የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በ72 ከተሞች ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12 /2013 (ኢዜአ) የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምን በ72 ተጨማሪ ከተሞች ለመተግበር በዝግጅት ላይ መሆኑን የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ገለፀ።

መርሃ ግብሩ እስከ መጪው ጥር የተጠቃሚዎች ልየታና የቢሮ አደረጃጀት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው የካቲት ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ኤጀንሲው አስታውቋል።

በአዲስ አበባም በሁለተኛ ምዕራፍ በሚተገበረው የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ከ109 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

በኤጀንሲው የዓለም ባንክ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃግብር አስተባባሪ አቶ ደበበ ባሩድ በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች በቀጥታ ድጋፍና በአካባቢ ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዓለም ባንክና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር በሚከወነው መርሃግብር የተመዘገበው ውጤት ባንኩ መርሃ ግብሩ እንዲሰፋ ድጋፍ እንዲያደርግ እንዳስቻለም ጠቁመዋል።

የቀደመው መርሃ ግብር የደሃ ደሃ የሆኑ ዜጎችን፤ የአሁኑ ደግሞ ስራ አጥ ወጣቶችና ስደተኞችን ታሳቢ ማድረጉን ገልፀዋል።

እንደ አቶ ደበበ ገለጻ ነባሮቹን 11 ጨምሮ በ83 ከተሞች የሚገኙ 780 ሺህ ዜጎች በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ለመርሃ ግብሩ ትግበራ የዓለም ባንክ 400 ሚሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ 150 ሚሊዮን ዶላር መድበዋል።

በዚህም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይ፣ በሱማሌ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በአፋር ክልሎች በተመረጡ 72 ከተሞች የሚገኙ የደሃ ደሃ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የሕዝብ ብዛት፣ የድህነት ምጣኔ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የበጀት ቀመርና የስራ አጥነት ምጣኔ  ለተመረጡት ከተሞች መመዘኛ መስፈርቶች እንደሆኑም ጠቁመዋል።

ክልሎች በዚሁ መሰረት ተጠቃሚ የሚያደርጓቸውን ከተሞች በራሳቸው መመዘኛ መምረጣቸውንም ገልፀዋል።

የልየታ ኮሚቴና አደረጃጀት ስራዎች እስከ መጪው ጥር ተጠናቀው መርሃ-ግብሩ ከየካቲት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናልም ብለዋል።

የአዲስ አበባ የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጀንሲ በበኩሉ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በሚተገበረው ሁለተኛው ምዕራፍ መርሃግብር ከ109 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብሏል።

የኤጀንሲው የከተማ ምግብ ዋስትናና ኑሮ ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን ሱልጣን እንዳሉት በመዲናዋ በመጀመሪያ ምዕራፍ መርሃ-ግብር ከ400 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

በከተማዋ የነበረውን አደረጃጀትና የልየታና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች በማጠናከር መርሃ-ግብሩ ወደ ትግበራ ይገባል ነው ያሉት።

በአገር አቀፍ ደረጃ በ72 ከተሞች የሚተገበረው መርሃ-ግብር ጥቅምት 16 እና 17 ቀን 2013 ዓ.ም በደሴ ከተማ  ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም