ቀጥታ፡

በ3ኛው ዙር 8100 A የገቢ ማሰባሰቢያ እጣ አሸናፊ መኪናቸውን ተረከቡ

አዲስ አበባ ጥቅምት 12 / 2013 ዓ/ም (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጭር የፅሁፍ መልዕክት የገቢ ማሰባሰቢያ 3ኛ ዙር ተሸላሚ መኪናቸውን ተረከቡ።

በ3ኛው ዙር 8100 A መልዕክት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡም ተገልጿል።

የእጣው አሸናፊ የሆኑት ወይዘሮ አሰፋሽ አፈወርቅ የመኪና ቁልፋቸውን በዛሬው እለት ተረክበዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት አባልና የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር  ዮሃንስ በንቲ" 8100 A አጭር  የጽሁፍ መልዕክት ለግድቡ ቦንድ መግዛት የማይችሉ ዜጎች የበኩላቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ እድል የፈጠረ" ነው ብለዋል።

የአገሪቱ ግዙፍ የልማት አጀንዳ ለሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።  

በአገር ውስጥና በውጪ  የሚኖሩ  ኢትዮጵያዊንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት አንስቶ እስካሁን ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዢና በልገሳ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የጽህፈት ቤቱ የኮሙንኬሽን ዳይሬክተር ሃይሉ አብረሃም ለግድቡ ግንባታ የቦንድ ግዢና ልገሳ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በ3ኛው ዙር 8100 A አጭር የጽሁፍ መልዕክት ብቻ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ገልጸዋል።  

በቀጣይም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው ህዝቡም ድጋፉን አንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የዛሬው የመኪና እጣ አሸናፊ በኦሮሚያ ክልል የኢሉአባቦር ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ  አሰፋሽ አፈወርቅ የመኪና ቁልፋቸውን በመቀበል ደስታቸውን ገልጸዋል። 

በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የቀድሞው የምድር ጦር ሠራዊት አባላትና ሲቪል ሰራተኛ ማህበር የ10 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም