በሐረሪ ክልል ከ40 በሚበልጡ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ከ40 በሚበልጡ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ ተጀመረ

ሐረር ጥቅምት 12/2013 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የመማር ማስተማር ስራ ገጠርና ከተማ በሚገኙ ከ40 በሚበልጡ ትምህርት ቤቶች መጀመሩ ተገለጸ።
የክልሉ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አዲስ አለም በዛብህ እና ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ ትናንት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመገኘት የተጀመረውን የመማር ማስተማር ሂደት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
አፈ ጉባኤዋ በወቅቱ እንደተናገሩት በክልሉ ገጠር እና ከተማ በሚገኙ የተወሰኑ የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ ተጀምሯል።
በተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶችም ኮሮና ቫይረስን በመከላከል የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማካሄድ አንፃር የተቀመጡ መመሪያዎችንና መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ እየተካሄደ ስለመሆኑ ተመልክተናል ብለዋል።
ኮሮናን በመከላከል የተጀመረው የትምህርት ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በበኩላቸው "እየተጋገዝን ኮሮናን በመከላከል የመማር ማስተማር ስራው በአግባቡ እንዲካሄድ ማድረግ ይገባናል" ብለዋል።
ኮሮናን በመከላከል የተጀመረው የመማር ማስተማሩ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በተለይ በመምህራን ላይ ያለውን ጫና ከመቀነስ አንፃር የትምህርት ባለሙያዎች እገዛ በማድረግ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተው "እኔም በፍቃደኝነት ለማስተማር ተዘጋጅቻለሁ" ብለዋል።
በክልሉ ከተማና ገጠር በሚገኙ 42 ትምህርት ቤቶች የስምንተኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለፈተና የማዘጋጀት ስራ መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ናቸው።
ትምህርት በተጀመረባቸው ሁሉም ትምህርት ቤቶችም የውሃ አቅርቦትና የእጅ መታጠቢያ፣ ሳኒታይዘርና ሙቀት መለኪያ በማሟላት በክፍል ውስጥ ተማሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲቀመጡ ጨምሮ አስፈላጊውን የጥንቃቄ መመሪያዎችን በአግባቡ እየተተገበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ 167 የመንግስትና ግል ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹም በቀጣይ እንደሚከፈቱ ተመልክቷል።
የክልሉ አመራሮችና የትምህርት ባለሙያዎችም በመምህራን ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስና እገዛ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የጀግኖች ትምሀርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ በረከት ለገሰ በሰጠችው አስተያየት ትምህርት በመጀመሩ ተደስቻለሁ ኮሮና ቫይረስን በመከላከል ትምህርቴን ለመቀጠልም ተዘጋጅቻለሁ ብላለች።