ቀጥታ፡

የዕርቀ ሠላም ኮሚሽኑ በሩብ ዓመቱ ከአጋር አካላት ጋር የትብብር ማዕቀፎችን መስርቷል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዕርቀ ሠላም ኮሚሽን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከአጋር አካላት ጋር የትብብር ማዕቀፎችን መመስረቱን አስታወቀ።

በተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ሳቢያ በሕዝቦች መካከል የተፈጠሩ ቁርሾዎችን በማከም እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ ዕርቅ ማውረድ እንደሚያስፈልግ ይታመናል።

በኢትዮጵያም ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ እየተገነባ የሚሄድ ስርዓት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዕርቀ ሠላም ኮሚሽን የተለያየ አቋም የያዙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማወያየትና ለአገራዊ ዕርቅ መሰረት የሚሆኑ የጋራ መርሆዎችና እሴቶችን በመለየት የመፍትሄ ሃሳቦች በማስቀመጥ ይሰራል።

ኮሚሽኑ በዚህ ረገድ በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ከተውጣጡ አጋር አካላት ጋር የትብብር ማዕቀፎችን መመስረት እንደተቻለ ገልጸዋል።

በሩብ ዓመቱ ከሠላምና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር የትብብር ማዕቀፎች መፈረማቸውን አብነት ጠቅሰዋል።

ከሠላም ሚኒስቴር ጋር የተፈረመው ስምምነት በአቅም ግንባታና በመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች በጋራ መስራት የሚያስችል ማዕቀፍ መሆኑን ተናግራዋል።

ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ስምምነትም በጥናትና ምርምር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎትና የኮሚሽኑን ተደራሽነት ማስፋት ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

የጥናትና ምርምር ስራዎችን የሚመለከተው ስምምነት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በሚገኙ መምህራን አማካኝነት ኮሚሽኑ ከዕርቀ ሠላም ጋር የተያያዙ ምርምሮችን ማጠናቀርና ማካሄድ የሚያስችል ነው።

ሠላምና ዕርቅ ተኮር የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን ይበልጥ ለማቀናጀትና በ13 ዩኒቨርሲቲዎች የዕርቀ ሠላም ጽህፈት ቤቶችን ለመክፈት እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።

ፅህፈት ቤቶቹ የሚከፈቱት በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ፣ በአርባምንጭ፣ በአሰላ፣ በአሶሳ፣ በባህርዳር፣ በደሴ፣ በድሬዳዋ፣ በጋምቤላ፣ በጂግጂጋ፣ በሐዋሳ፣ በጅማና ነቀምቴ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሆነም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዕርቀ ሠላም ኮሚሽን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 28 ቀን 2011 ዓ.ም ባፀደቀው አዋጅ ቁጥር 1102/2011 የተመሰረተ ነጻና ገለልተኛ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም