ቀጥታ፡

የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ሠራተኞች ደም ለገሱ

አዲስ አበባ   ጥቅምት 12/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የአመራር አባላትና ሠራተኞች ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል መርህ ዛሬ ደም ለግሰዋል፡፡

የደም ልገሳው ዓላማ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን እጥረት ማቃለል መሆኑን የድርጅቱ የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቡድን መሪ ወይዘሮ እታገኝ ተካልኝ ገልፀዋል።

ወላድ እናቶችና ሕፃናት በደም እጦት ለሞት እንዳይዳረጉ  የበኩላቸውን ለማበርከት ደም እንደለገሱ  የድርጅቱ ሠራተኞች ተናግረዋል።

በደም ልገሳው የተሳተፉት የተቋሙ ሠራተኞችም ችግር ያጋጠማቸውን ወገኖች መደገፍ በመቻላቸው ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለሶስተኛ ጊዜ ደም የለገሱት ወይዘሮ ምሕረት ሕሉፍ ዜጎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሳይዘናጉ የሌሎችን ሕይወት ለመታደግ ደም እንዲለግሱ ጠይቀዋል።

በደም ልገሳው ለሁለተኛ ጊዜ መሳተፋቸውን የገለፁት አቶ ኤልያስ ኢዶሳም ደም በመለገስ ወገኖቻችንን ልናግዝ ይገባል ብለዋል።

ለካንሰር ሕሙማን፣ ለድንገተኛ አደጋዎችና ለወላድ እናቶች በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ደም እጅግ እንደሚያስፈልግ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም ባንክ ከለጋሾች የሚያገኘው ደም ከፍላጎቱ አንፃር በቂ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ይገልፃል።

ደም በተፈጥሮው የመጠቀሚያ ጊዜው አጭር በመሆኑ ያለማቋረጥ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግና ለዚህም በርካታ ለጋሾች እንደሚያስፈልጉም እንዲሁ።

እናም አሁን ባለው ሁኔታ የአካል መራራቅ ሒደትን ጠብቆ ደም መለገስ ይቻላል ነው የተባለው።

በብሔራዊ ደም ባንክ መረጃ መሠረት የአገሪቷ ዓመታዊ የደም ፍላጎት አንድ ሚሊዮን ዩኒት ያህል ቢሆንም በየዓመቱ ከለጋሾች የሚገኘው ከ223 ሺህ ዩኒት አይበልጥም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም