ቀጥታ፡

በሐረር ከተማ የድንገተኛ እና ጽኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻያ ፕሮግራም ተጀመረ

ሐረር ጥቅምት 12/2013 (ኢዜአ) በሐረር ከተማ የድንገተኛ እና ጽኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻያ የጤና አገልግሎት ፕሮግራም ተጀመረ።

ፕሮግራሙ ሐረርን ጨምሮ በምስራቁ የሀገሪቱ  ክፍል በተቆራረጠ ሁኔታ  የሚከናወኑ የድንገተኛ አደጋና ጽኑ ህሙማን እንክብካቤና አገልግሎት አሰጣጥ ወጥና ተቋማዊ  እንዲሆን እንደሚያደርግ ተመልክቷል።

ፕሮግራሙን ትናንት በይፋ ያስጀመሩት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር  አቶ ኦርዲን በድሪና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ጉዳይና የአስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጀይላን ወልይ ናቸው።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተመረጡ አምስት የድንገተኛና ጽኑ ህሙማን እንክብካቤና ማሻሻያ አገልግሎት መስጪያ ፕሮግራሞች  መካከል የሐረሩ አንዱ ነው።

የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን ህክምና አገልግሎት ከዚህ ቀደም  ትኩረት ያልተሰጠውና ክፍተት የነበረበት መሆኑን ጠቁመው  በአሁኑ ወቅት ግን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆስፒታሎችና ሌሎች ጤና ተቋማት በአገልግሎቱ አሰጣጥ የሚታዩ ክፍተቶችን በቴክኖሎጂ፣ ሰው ኃይል እና ግብአት የማጠናከር ስራ ይከናወናል፤ የክልሉ መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት የህክምና ተቋማትን በማስፋፋትና ጥራትን በማሻሻል የአገልግሎት አሰጣጡን እያጎለበተ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህም አሁን ለተጀመረው የድንገተኛና ጽኑ ህሙማን እንክብካቤና ማሻሻያ አገልግሎት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በተለይ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  በከተማው በህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ቲቺንግ ሆስፒታል ግንባታው እየተጠናቀቀ የሚገኘውና 100 የህሙማን አልጋ ያለው ዘመናዊ የህክምና ህንጻ  ለምስራቅ ኢትዮዽያ የህክምና አገልግሎት  በመስጠት ሐረርን የህክምና ቱሪዝም ሴንተር እንደሚያደርጋት ጠቅሰዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ዲን ዶክተር ያደታ ደሴ በበኩላቸው ድንገተኛ አደጋዎች  በተሸከርካሪ ፣ እሳት፣ግጭትና በሌሎችም  ሰው ሰራሽና ተፈጥሮ ችግሮች  የሚከሰቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህ ምክንያት ችግሮቹ ሲከሰቱ  ፕሮግራሙ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኝ ህዝብ በህይወት ፋና ሆስፒታል አገልግሎቱን ለመስጠት ስራውን በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ምስራቅ ሐረርጌ የተሸከርካሪ አደጋ  የሚበዛበት ዞን መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ  ጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት  ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ አብዱረሃማን ናቸው።

የፕሮግራሙ  መጀመር በአደጋው ጉዳት የሚደርስባቸውን ሰዎች ለመታደግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

እንዲሁም በጤና ጣቢያ የሚታይ መጨናነቅ፣ ንብረትና የሰው ሃብት በአግባቡ ለመጠቀምና የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሹም አቶ በቀለ ተመስገን በበኩላቸው የፕሮግራሙ መጀመር ሐረርን ጨምሮ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል በተቆራረጠ ሁኔታ የሚከናወኑ የድንገተኛ አደጋና ጽኑ ህሙማን እንክብካቤና አገልግሎት አሰጣጥ ወጥና ተቋማዊ  እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።

ፕሮግራሙ ሲጀመር  የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፣  የሐረማያ ዩኒቨርሲቱ መምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም