በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር የሚገኙ 11 ተቋማት የጋራ ዕቅድ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር የሚገኙ 11 ተቋማት የጋራ ዕቅድ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 12/2013(ኢዜአ) በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር የሚገኙ 11 ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ተግባር በመፈጸም ችግሮችን በጋራ መፍታት የሚያስችላቸውን የጋራ ዕቅድ ስምምነት ተፈራረሙ።
በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን አስተባባሪነት የተካሄደው የጋራ ዕቅድ ስምምነቱ የተጠያቂነት ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስችል ተገልጿል።
ተቋማቱ የጋራ ዕቅዶቻቸውን መፈጸምና በቅንጅት መስራት በሚያስችላቸው ሰነድ ላይ ውይይት አካሂደዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት፣ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲና ኢንስቲትዩት፣ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት፣ የብረታብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፤
እንዲሁም የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት አቅራቢ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የቆዳ ልማት ኢንዱስትሪ ልማት፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ልማት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩትና የምግብ መጠጥና ፋርማሲቲካል ልማት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት ናቸው።
የአቅም ግንባታ ስራዎች፣ የጥራትና ደረጃዎች እና የምርት ግብዓት አቅርቦትና የገበያ ትስስር መፍጠር፤ ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስርዓት መዘርጋትና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማሸጋገር ደግሞ በተቋማቱ በጋራ የሚተገበሩ ዋና ዋና ግቦች ናቸው ተብሏል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረእየሱስ ስምምነቱ "ተቋማቱ በዕቅድ የያዟቸውን ተግባራት በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ በትብብር እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል" ብለዋል።
አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ለአገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ካላቸው ሚና አንጻር
ተቋማቱ ያስቀመጧቸውን ግቦች በመፈጸም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበም ተቋማቱ የጋራ ዕቅዳቸውን በትብብርና በተጠያቂነት መንፈስ መፈፀማቸው "የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ዕድገት እንዲያስመዝገብ ያደርጋል" ብለዋል።
የጋራ ዕቅድ ፊርማው ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን ተግባር በመፈጸም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችም በጋራ መፍታት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የተቋማቱ የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮችም ስምምነቱ በጋራ ያስቀመጧቸውን ዕቅዶች በቅንጅት ለመፈጸም ስላለው አስፈላጊነት ተናግረዋል።
ስምምነቱ ኃላፊነትን መውሰድ ስለመሆኑ ያነሱት ኃላፊዎቹ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የአገር ኢኮኖሚ እንዲደግፍና ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ዕቅዳቸውን በተጠያቂነት መንፈስ ለመፈጸም እንደሚያግዛቸው አብራርተዋል።
የጋራ ዕቅድ ስምምነቱ የታቀዱ ተግባራትን በመፈጸም ቅንጅታዊ አሰራርን እንደሚያጠናክርም ተገልጿል።