የድንቅ- ጨልጨል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድንቅ- ጨልጨል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ ነው
ጎባ፣ ጥቅምት 12/2013 ኢዜአ በምስራቅ ባሌ ዞን 2 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የድንቅ- ጨልጨል የመስኖ ልማት ፕሮጄክት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የፕሮጀክቱ አማካሪ አቶ ግርማ ይርጋ ፕሮጀክቱ በሶስት ዓመት ለማጠናቀቅ ውል ተገብቶ እየተገነባ ይገኛል ብለዋል፡፡
የግንባታ ስራው በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝና የኦሮሚያ ውኃ ስራዎች ኮንስትራክሽን በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ተቋራጮቹ የማሽነሪ አቅርቦት ችግርና ከአቅም ውስንነት ጋር በተያያዘ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ፍጥነት እየተገነባ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዚህም የግንባታ ሂደት በአሁኑ ወቅት 30 በመቶ መጠናቀቅ ሲኖርበት በአማካይ 9 በመቶ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ችግሩን በማስመልከት ለፕሮጀክቱ ተቋራጮች ለስራው አስፈላጊ የሆኑ ማሽነሪዎችና የሰው ኃይል በማንቀሳቀስ ግንባታውን በማፋጠን አጠናቀው ለአገልግሎት እንዲያዘጋጁ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አማካሪው ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱን በበላይነት የሚቆጣጠረው የፌዴራል መስኖ ልማት ኮሚሽን መሆኑን ጠቁመው ለግንባታም የፌዴራል መንግስት 2 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር መመደቡን አመልክተዋል።
የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ተወካይ አቶ አበራ ሲሳይ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ኮንትራት ዘግይቶ መጀመሩና የግብዓት አቅርቦት ውስንነት ለግንባታው መጓተት በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡
በአካባቢው የሚገኙ የግንባታ እቃዎችን በመጠቀምና አስፈላጊውን የግንባታ ማሽን በማንቀሳቀስ በሙሉ አቅማቸው በመስራት ፕሮጄክቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ሌተ ቀን እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት የተጓተተና በሙሉ አቅማችን እንዳንሰራ የሲሚንቶ አቅርቦት ማነቆ ሆኖብናል ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ተወካይ አቶ ጫላ ስሜ ናቸው።
የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር በመንግስት በኩል እንዲፈታላቸው ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ያመለከቱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በድርጅታቸው ደረጃ ማሟላት የሚገባቸውን በመፈጸም ስራውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እንደሚረባረቡ ገልጸዋል፡፡
የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደም ቃሲም በበኩላቸው መንግስት የአካባቢውን አርብቶ አደር የምግብ ዋስትና ችግርን ለማቃለል ለመስኖ ልማት ትኩረት ሰጥትቶ እየሰራ ነው ብሏል፡፡
አርብቶ አደሩ በምግብ እህል እራሱን እንዲችል በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ የሚኖረው የድንቅ-ጨልጨል ፕሮጀክት ግንባታ ከግቡ እንዲደርስ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ የግንባታውን ስራ ያስጀመሩት የድንቅ -ጨልጨል የመስኖ ልማት ፕሮጄክት በተያዘለት ሶስት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ከ4ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት አቅም ይኖረዋል።
8ሺህ ያህል አባወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ከፕሮጄክቱ አማካሪ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡