ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ 16 የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ሊከፍት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ 16 የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ሊከፍት ነው
ሆሳዕና፣ ጥቅምት 12/2013 (ኢዜአ) በተያዘው የትምሀርት ዘመን 16 አዳዲስ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ሊከፍት መሆኑን ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።
በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተመስገን ቶማስ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፕሮግራሞችን ለመክፈት የሥርዓተ ትምህርት ግምገማዎችን በማካሄድ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጓል።
በተያዘው ዓመት ከሚከፈቱት 16 አዳዲስ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች መካከል ማስተርስ ኦፍ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ፣ ካምፒውተር ሣይንስ፣ ጂኦ ኢንፎርማቲክስ፣ ሪፕሮዳክቲቭ ሄልዝና ኤጁኬሽን ኤንድ ፕሮሞሽን የትምህርት ዓይነቶች እንደሚገኙባቸው ጠቅሰዋል።
እንደ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገለፃ ሥርዓተ ትምህርቶቹ ከመዘጋጀታቸው አስቀድሞ ያላቸው ሀገራዊ ጠቀሜታ እንዲሁም የገበያ አዋጭነት በጥናት ተረጋግጧል።
በተለይ መንግሥት የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ለማብቃትና የትምህርት ዝግጅታቸውን ለማሳደግ ለሚያደርገው ጥረት በነዚህ የትምህርት መስኮች ተመርቆ የሚወጣው የሰው ኃይል ክፍተቱን ለመሸፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
እንደ አዲስ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ማስፋፋት የተቋሙ ዋነኛ እቅድ እንደሆነ አመልክተው፤ ይህም ሀገራዊ ተልዕኮ ከማሳካትና ከዩኒቨርሲቲው ዕቅድ አንፃር እንደ ትልቅ ስኬት እንደሚታይ ዶክተር ተመስገን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው እስካሁን ሲሰጥ የነበረውን 15 የድኀረ ምረቃ ፕሮግራሞች አዲስ የሚከፈቱት ሲጨመር ከእጥፍ በላይ እንደሚሆን አስታውቀዋል።
ተቋሙ በእውቀትና ክህሎት ብቁ የሆነ ዜጋን ለመፍጠር የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት እየሰራ እንደሚገኝ ዶክተር ተመስገን አብራርተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃ ትምህርት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ካቻ አሰፋ በበኩላቸው በሚከፈቱት ፕሮግራሞች ከ500 በላይ የድኀረ ምረቃ ተማሪዎችን በመቀበል ለማስተማር ምዝገባና የመግቢያ ፈተና ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በ2012 የትምህርት ዘመን በመደበኛና በተከታታይ የትምህርት ፕሮግራሞች ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎች ሲያስተምር መቆየቱ ተመልክቷል።