ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ጅቡቲ የዕንባ ጠባቂ ተቋማት በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12 /2013 ዓ.ም (ኢዜአ)  የኢትዮጵያና ጅቡቲ የእንባ ጠባቂ ተቋማት በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ እና የጅቡቲ የዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር ቃሲም ኢሳቅ ስምምነቱን ዛሬ ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ እንዳሉት ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በጋራ መስራት የሚያስችላቸው ነው።

አገራቱ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክርና በተለያዩ መስኮች ተቀራርበው እንዲሰሩ ከማድረግ አንጻርም ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

የጅቡቲ የዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር ቃሲም ኢሳቅ በበኩላቸው በስምምነቱ መሰረት የሁለቱ ተቋማት ባለሙያዎች የልምድ ልውውጦችን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ በጅቡቲ የስራ ጉብኝት እንዲያደርጉም በዶክተር ቃሲም ግብዣ ቀርቦላቸዋል።

የጅቡቲ የዕንባ ጠባቂ ተቋም እ.አ.አ በ1999 የተቋቋመ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ደግሞ በ1991 ዓ.ም የተቋቋመ መሆኑ ይታወቃል።

ተቋሙ በሕግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶችና ጥቅሞች በአስፈፃሚው አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ጥራት፣ ቅልጥፍና እና ግልጽነት ያለው መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ ዋና አላማው አድርጎ ይሰራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም