በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄዱ ለውጦችን የዳሰሰ መፅሐፍ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄዱ ለውጦችን የዳሰሰ መፅሐፍ ተመረቀ
አዲስ አበባ ጥቅምት 12/2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ የተከናወነውን የፖለቲካ ለውጥ ሂደትና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚያመላክት መጽሐፍ ለምረቃ በቅቷል።
መጽሐፉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ "ETHIOPIA in the WAKE of POLITICAL REFORM" በሚል ርዕስ በአራት ክፍሎችና በ616 ገጾች የተዋቀረ ነው።
በ20 ምሁራን የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ በአገሪቷ ባለፉት ሁለት ዓመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የተካሄደውን ለውጥ የዳሰሰ መሆኑ ተገልጿል።
ኅብረተሰቡ ስለ ለውጡ ያለውን ግንዛቤና የለውጡን ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ያመላከተ ሰለመሆኑም ተነግሯል።
የፌዴራሊዝም፣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ሌሎችም በመጽሐፉ ሽፋን ያገኙ ሀሳቦች ናቸው።
በመጽሐፉ ሥራ ከተሳተፉት ምሁራን አንዷ ዶክተር ስህን ተፈራ በለውጡ ሂደት ፆታና የፆታ እኩልነት የተመለከተ አንድ ምዕራፍ ጽፈዋል።
በለውጡ ሂደት ውስጥ ሆኖ ለውጡን የሚተችና ግምገማ የሚሰጥ መጽሐፍ መውጣቱ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው ዶክተሯ ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ አማካሪና የመጽሐፉ ተባባሪ አርታኢ አቶ ምህረቱ ማሞ መጽሐፉ ለውጡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምን እንደሚመስል ትንታኔ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
የሽግግር ምንነት፣ የመደመር ፖሊሲን ግብና ውጤት ጨምሮ በለውጡ በመንግሥት የተወሰዱ የሚዲያና የሲቪል ማኅበረሰብ ነፃነትን የተመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮችን መመልከቱን ተናግረዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ የነበሩ ስብራቶችና የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን መዳሰሱንም ገልጸዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ መርዕድ ስለ መጽሐፉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ፕሮፌሰር በየነ መጽሐፉ መንግሥት ከማወቅ ተነስቶ ፖሊሲዎቹን እንዲያስተካክል ይረዳዋል ብለዋል።