ብዝሃነትን መሰረት ያደረገ የሰላም ግንባታ የሰውን መብት ለማስጠበቅ የጎላ ድርሻ አለው - ኢዜአ አማርኛ
ብዝሃነትን መሰረት ያደረገ የሰላም ግንባታ የሰውን መብት ለማስጠበቅ የጎላ ድርሻ አለው
ጅማ፣ ጥቅምት 11/2013 (ኢዜአ) ብዝሃነትን መሰረት ያደረገ የሰላም ግንባታ የሰውን ተፈጥራዊና ህጋዊ መብት ለማስጠበቅ የጎላ ድርሻ ያለው መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር በአብሮነትና ብዝሃነት አያያዝ ዙሪያ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ በጅማ ከተማ ተካሄዷል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በመድረኩ እንዳሉት በጅማ አካባቢው ግጭትን ለመከላከል ባለፉት ዓመታት በተከናወነው ስራ የተሻለ የአብሮነትና ብዝሃነት አያያዝ ልምድ ተገኝቷል፡፡
ውይይቱ የተዘጋጀውም ይህን ልምድ ለሌሎች አካባቢዎች በሚደርስበት ሁኔታ ላይ ለመመክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሰላምና ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘሪሁን አሰፋ በውይይቱ ባቀረቡት ጽሁፍ ብዝሃነት የሰው ልጅ ተፈጥራዊ ባህሪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ብዝሃነት ከግለሰብ ባለፈ በቤተሰብ ፣አካባቢ፣ አጠቃላይ ያለና ወደፊትም የሚኖር እውነታ መሆኑን ለተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ይህን እውነታ በመረዳት ብዝሀነታችንን ለሰላም መደፍረስ ምክንያት አድርገነው የታሪክ ተወቃሽ ልንሆን አይገባም ብለዋል፡፡
ከጅማ ዞን ኦሞ ናዳ ወረዳ የተሳተፉት ወይዘሮ ማሾ አባዱራ የሰላም ግንባታ በእኩልነት ተከባብሮ ለመኖር የሚያስችል እሴት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አንጻር በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት እየተፈጠረ ያለው ችግር ለሰው ልጅ ክብር ትኩረት የማይሰጡ አካላት ብዝሃነትን ተጠቅመው የሚፈጥሩት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህን መከላከል የሚቻለው የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋም እንደሚያደርገው ሌሎች አካላትም በብዝሃነት አያያዝ ላይ ንቃተ ህሊናው የዳበረ ህብረተሰብ ለመፍጠር ሲያግዙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ወጣት ይዘዲን ከማል በበኩሉ ብዝሃነት በግለሰብ፣ ቤተሰብ ፣አካባቢ፣ ተፈጥሮ ውስጥ ያለና ልንቀበለው የሚገባ እውነት ነው ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ብዝሃነትን ከመቀበል ይልቅ የኔ የተሻለ ባህል፣ ታሪክ፣ ኃይማኖት አለኝ ወደሚል አላስፈላጊ ክርክር ውስጥ በመገባቱ የአብሮነትንና ብዝሃነት አያያዝ ጉዳይ ችግር እየገጠመው መሆኑን ከውይይቱ መገንዘብ እንደቻለ ገልጿል፡፡
ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በመሳተፍ የድርሻውን እንደሚወጣም ተናግሯል፡፡
የጅማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን ጆቢር በበኩላቸው" የሀገራችንም ሆነ የከተማችን የብዝሃነት ጉዳይ ሚዛኑን የጠበቀና የተስተካከለ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል "ብለዋል፡፡
ሁሉንም የሀገሪቱን ችግር በመንግስት ብቻ መፍታት ስለሚያዳግት በኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እገዛ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡