በአማራ ክልል የሚገኙ የዩኒቨርሲቲዎች ፎረም አንበጣን ለመከላከል ከ12 ሚሊዩን ብር በላይ ድጋፋ አደረገ

ደብረ ማርቆስ፣ ጥቅምት 11/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በምስራቅ አማራ ሰብላቸው በአንበጣ መንጋ ለጠፋባቸው አካባቢዎች 12 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የፎረሙ ሰብሳቢ ዶክተር ታፈረ መላኩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ዩኒቨርስቲዎች ከማስተማር ስራቸው በተጓዳኝ በማህበረሰብ አገልግሎት መሳተፍ ዋና ተልኳቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የአንበጣ መንጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ከማህብረሰቡ ጋር ተቀናጅተው በመከላከል ላይ በመሳተፍ አጋርነታቸውን እያሳዩ ናቸው ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረምም ከራሱ በጀት በመቀነስ 12 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በምስራቅ አማራ ሰብላቸው በአንበጣ ለወደመባቸው አካባቢዎች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ፎረሙ ያደረገው ድጋፍም አንበጣውን ለመከላከል የሚያግዙ ግብአቶችን ለመግዛት እና ለማህበረሰቡ የምግብ ፍጆታ ለማቅረብ የሚውል መሆኑን  ዶክተር ታፈረ አስረድተዋል።

ድጋፉም በክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤትና ግብርና ቢሮ አማካኝነት ለተጎዱ አካባቢዎች እንደሚደርስም አመልክተዋል።

የዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ግብርናውን በማዘመንና የሚከሰቱ አደጋዎች በመከላከል ላይ ያተኮረ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለማገዝ አተኩሮ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

ፎረሙ በአማራ ክልል የሚገኙ አስር ዩኒቨርሲቲዎችን በአባልነት አካቶ ለክልሉ ሁለንተናዊ ልማት አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም