ቀጥታ፡

ማዕከሉ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በማሰራጨት ከ500 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አደረገ

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 11/2013 (ኢዜአ) አዲሱ የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማዕከል ባሳለፍነው የክረምት ወቅት የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በማሰራጨት ከ500 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ።

ማዕከሉ በቀጣይ በገብስ፣ የስንዴና የደጋ በቆሎ ሰብሎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጿል።

ማዕከሉ የብቅል ገብስ፣ የጤፍና ስንዴ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮቹ ያሰራጨው በ241 ሄክታር ማሳ በማባዛት እንደሆነም አመልክቷል።

በአንጋፋው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥር በመላ አገሪቱ ከተቋቋሙ የምርምር ማዕከላት ዘግይቶ የተቋቋመ ነው በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኘው የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማዕከል።

በየካቲት 2011 የተቋቋመው ማዕከል ለደጋና ወይናደጋ ሥነ ምህዳር ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ፣ ማላመድ፣ ማስተዋወቅ፣ ዘር ብዜትና ስርጭት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።

ማዕከሉ በእስካሁን የምርምር ተግባራቱ ካከናወናቸው ሥራዎች መካከል በሰብል ምርምር ላይ ያከናወናቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የምርምር ተቋማት ባለሙያዎችን ያካተተ ልዑክ  ተመልክቷል።

የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ያለው ማዘንጊያ ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከሉ በሰብል፣ እንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ በድምሩ ከ70 በላይ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ከነዚህም ውስጥ በሰብል ምርምር በ2012/2013 በጀት ዓመትም በደጋና ወይናደጋ ብርዕና አገዳ ሰብሎች፣ በጥራጥሬ፣ በቅባት ሰብሎች፣ በአግሮኖሚና ፍራፍሬ በአጠቃላይ 29 ምርምሮችን በማዕከሉ የምርምር ስፍራ እያካሄደ ነው።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ የአፈር አሲዳማነት ያጠቃው አካባቢ በመሆኑ የአፈር ለምነትን በመመለስና በሌሎች የምርምር ማዕከላት የወጡ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በማሰራጨት ለአርሶ አደሩ የማስተዋወቅ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በጎዛምን፣ በስናን፣ በደብረ ኤልያስ፣ በአነደድና በአዋበል ወረዳዎች በሰባት ኩታገጠም ማሳያዎች ላይ ልማቱን እያካሄደ ነው ብለዋል።

በዚህም በዳቦ ስንዴ፣ የብቅል ገብስ፣ የደጋ በቆሎና የጤፍ ምርጥ ዘር እና የአፈር አሲዳማነት ማከሚያ ኖራ ለአርሶ አደሮች በነጻ መቅረቡን ገልጸዋል።

ከነዚህም መካከል ከ336 ኩንታል በላይ የብቅል ገብስ፣ የዳቦ ስንዴና የጤፍ ዝርያዎችን በማሰራጨት 545 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ማዕከሉ ከሰብል ምርምር በተጨማሪ በተፈጥሮ ሃብት አያያዝ እንዲሁም በወተት ከብት፣ በእንስሳት መኖ፣ በበግና ዶሮ ምርምሮችን ጀምሯል ብለዋል።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሙላቱ ካሳዬ ዩኒቨርሲቲው ከማዕከሉ ምስረታ ጀምሮ በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱንና በአጭር ጊዜ ተጨባጭ ውጤቶች ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

በዳቦ ስንዴና በብቅል ገብስ በድምሩ ለ150 ሄክታር ማሳ የሚሆን ኖራ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ገዝቶ ማቅረቡን አስታውቀዋል።

ወደፊትም ከማዕከሉና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ተሳትፎውን ያጠናክራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የጥናትና ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ድሪባ ገለቲ በኢንስቲትዩት ስር የሚገኘው የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማዕከል ''በአጭር ጊዜ ውጤታማ የግብርና ስራዎችን ያከናወነ'' ብለውታል።

ሰፊ የሰብል ምርት የሚመረትበት የምሥራቅ ጎጃም አካባቢ ከዚህ በፊት የምርምር ማዕከል እንዳልነበረው ገልጸው፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ማዕከሉ በመቋቋሙና ባከናወናቸው ሥራዎች ደስተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ማዕከሉ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ መስራቱም የምርምር ተቋማት በጋራ ሲሰሩ አመርቂ ውጤት እንደሚያመጡ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።

በቀጣይ ማዕከሉ አስፈላጊ ግብዓቶች ተሟልተውለት በተለይም ደጋማ አካባቢ ሰብሎች እንደ ገብስ፣ ስንዴና የደጋ በቆሎ ዝርያዎች ላይ የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ይሰራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም