ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ መጥፋትና የኃይል መቆራረጥ በገቢያችን ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል-- ደንበኞች

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 11/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ መጥፋትና የኃይል መቆራረጥ ገቢያቸውን እንደጎዳባቸው ደንበኞች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት በየጊዜው የሚጠፋውና እየተቆራረጠ የሚደርሳቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በሥራቸውና በገቢያቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አቦወርቅ አበራ የክሊክ ሱፐር ማርኬት ሥራ አስኪያጅ በየጊዜው በሚቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክንያት በጄኔሬተር ለመጠቀም መገደዳቸውን ይናገራሉ።

''መብራት በተደጋጋሚ ስለሚጠፋና ሄዶ ሁለት ቀን ሶስት ቀን ስለሚቆይ የሚበላሹ ዕቃዎች ስለምንይዝ በጄኔሬተር ነው የምንጠቀመው። ይሄም ላልተገባ ወጪ ዳርጎናል። ለሚመለከተው አካል ጉዳዩን እልባት እንዲሰጡ ብንጠይቅም፤ ምንም አይነት ምላሽ ማግኘት አልቻልንም’’ብለዋል።

አቶ ሀብቶም ገብረህይወት  በጎሚስታ ሥራ የሚተዳደሩ ግለሰብ  ናቸው።

በኤሌክትሪከ አቅርቦት ባለመስተካከሉ ገቢያቸውን ከመጉዳቱ በላይ፤በንብረታቸው ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ተመስገን ኃይለማርያም የአያት የመኪና ፍተሻ ሥራ አስኪያጅ በኤሌክትሪክ አገልግሎት ያለመስተካከል በሥራቸው ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ''ያለ ምንም ሥራ የቤት ኪራይ እየከፈሉ'' መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በከተማዋ የተሳለጠና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት ኔትወርኩን ማዘመንና የመልሶ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ይገልጻሉ።

ነባር መሥመሮችን በአዲስ ለመቀየር በሚደረግበት እንቅስቃሴና እየለሙ ባሉ መንደሮች በአገልግሎቱ ያሉትን ችግሮች ለማቃለል እየተሰራ ነው ብለዋል ።

የኃይል መቆራረጥ ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ኔትወርኩን የማሻሻልና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ሲጠናቀቁ ችግሩ እንደሚቃለል ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ሥራው ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ በትዕግስት እንዲጠብቅ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም