ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብትን ለማስከበር በሚደረጉ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮች በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ናት... ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብትን ለማስከበር በሚደረጉ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮች በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ናት... ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብትን ለማስከበር በሚደረጉ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮች በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።
የአፍሪካ አገሮች የሰዎችን ሰብአዊ መብት ለማስከበር የራሳቸውን ተቋማዊ አደረጃጀትና አህጉራዊ ትስስርን በመፍጠር በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የአፍሪካ ሰብአዊ መብት ቀንን ምክንያት በማድረግ ከአፍሪካ ህብረትና ከተለያዩ አካላት ጋር በበይነ መረብ ውይይት ካሂዷል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በውይይቱ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል እያደረገች ያለውን ተግባር አጋርተዋል።
አገሪቱ የህግ፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና ሌሎች ማሻሻያዎችን በማድረግ ለሰብአዊ መብት መረጋገጥ በለውጥ ሥራ ውስጥ መሆኗን በማብራሪያቸው ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያ እንደሌሎች ሥራዎች ሁሉ በሰብአዊ መብትም አህጉራዊ ትብብሮችን በማጠናከር ትሰራለች" ብለዋል።
ኮሚሽኑ እያደረገ ባለው የለውጥና የማሻሻያ ሥራ የአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሙያዊ ምክር በመስጠት ቁልፍ አጋር መሆኑንም ዶክተር ዳንኤል ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለሰብአዊ መብት መከበር በሚደረጉ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮች በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርን ወክለው በውይይቱ የተሳተፉት የሕብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሚናታ ሳማቲ በበኩላቸው የአፍሪካ ህብረት ሰብአዊ መብትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ቻርተሮችና ስምምነቶች እንዳሉት አውስተዋል።
የአፍሪካ አባል አገሮች ይህንን መሰረት አድርገው የራሳቸውን አገራዊ አሰራር፣ ህግና ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር መተግበር እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያመለከቱት።
"ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብትና የፍትህ ተቋማትን በማደራጀት እያከናወነች ያለው ተግባር ለሌሎች አርአያ ይሆናል" ብለዋል ኮሚሽነር ሚናታ ሳማቲ።
እንደ እሳቸው ገለጻ የአፍሪካ አገሮች የሰዎችን ሰብአዊ መብት ለማስከበር የራሳቸውን ፖሊሲ ከማውጣትና ተቋማዊ አደረጃጀት ከመፍጠር ባለፈ አህጉራዊ ትብብር በመፍጠር በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
አህጉራዊ ትብብርን በመፍጠር ሰብአዊ መብት የተከበረባት አፍሪካን እውን ለማድረግ ያለውን ሚና በመግለጽ አገሮች የራሳቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሰብአዊ መብትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ መርሃ ግብሮች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሲቪል ማህበራትና የሰብአዊ መብት ተሟጓቾች የድርሻቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
በውይይቱ በአፍሪካ የአዛውንቶች፣ ህጻናት፣ ሴቶችንና አጠቃላይ የሰብአዊ መብትን ለማረጋገጥ የተደረጉ ስምምነቶች፣ ቻርተሮችና ሌሎች ህጎች በቁርጠኝነት መተግበር እንዳለባቸው ተነስቷል።
የሲቪል ማህበራት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግስታት (ኢጋድ) እና ሌሎች በሰብአዊ መብት ላይ የሚሰሩ ተቋማት እያከናወኑ ያለውንም ተግባር በውይይቱ አጋርተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤን በቀለ፣ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ተወካይ፣ የኢጋድ ተወካይ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጓቾች፣ የሲቪል ማህበራትና ሌሎች በበይነ መረብ በተካሄደው ውይይትተሳትፈዋል።