ቀጥታ፡

የከተሞችን መስፋፋት አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል ግልጽና ዘመናዊ ፕላን ያስፈልጋል-- የመንግስታቱ ድርጅት

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 11/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የከተሞች መስፋፋት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር ግልጽና ዘመናዊ የከተሞች ፕላን ማዘጋጀት እንደሚገባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የከተሞች ኤጀንሲ ገለጸ።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በከተሞች ልማትና እድገት ላይ ከሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በኢትዮጵያ የከተሞች መስፋፋት ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

የዓለም ከተሞች ሶስት በመቶ የመሬት የአካል ላይ የተመሰረቱ ቢሆንም የኢኮኖሚውን 70 በመቶ ድርሻ የያዙ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የከተሞች ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ኃላፊ አክሊሉ ፍቅረስላሴ ለኢዜአ እንዳሉት በኢትዮጵያ ከተማነት በፈጣን እድገት እየተስፋፋ ነው።

በኢትዮጵያ ከተሜነት በየዓመቱ አምስት በመቶ በሆነ ፈጣን እድገት እየተስፋፉ ቢሆንም ግልጽና ዘመናዊ የከተማ ፕላን ባለመኖሩ ለችግር ሲጋለጡ ይስተዋላል ብለዋል።

የቆሻሻ አወጋገድ የትራንስፖርት አቅርቦትና የቤቶች ግንባታ በከተማ ነዋሪው ቅሬታ የሚቀርብባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከተሞች እንዴት፣ መቼ፣ ለምንና በምን መመራት እንዳለባቸው የሚያሳይ ግልጽ አሰራር ሊኖራቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል።

"ከተሞች ሲስፋፉ መሬት ላይ ህንጻዎችን መደርደር ብቻ በቂ አይደለም" የሚሉት አቶ አክሊሉ አላማቸውና ለነዋሪው የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በጥናት መታወቅ አለበት ብለዋል።

በየዓመቱ አምስት በመቶ ፈጣን እድገት እየተመዘገበበት ያለ የከተማነት መስፋፋት በዘመናዊ ፕላን መመራት ካልቻለ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለዋል።

ኤጀንሲው በአዲስ አበባና ባህር ዳር ከተሞች በቆሻሻ አወጋገድ እንዲሁም በሀዋሳ በፓርኮች ፕላን አዘገጃጀት ላይ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሁሉም ከተሞች በፖሊሲና በፕላን መመራት እንዲችሉ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በከተማ ሴፍትኔት ታቅፈው የነበሩ ከተሞችን ከ11 ወደ 80 ማሳደግ መቻላቸውን ገልጸዋል።

የከተሞች በከተማ ሴፍትኔት መርሃ ግብር መታቀፍ የከተሞቹ መስፋፋት በእቅድና በፕላን የተመራ እንዲሆን ያግዛል ብለዋል።

ለዚህም ከሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተዋንያን በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሰራሩና አካሄዱ በመንግስት መመራት ስላለበት የዘርፉን ተቋማት ተሳትፎ በየጊዜው እየተገናኘን እንገመግማለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም