ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ ኮቪድ-19 ከሥርዓተ ምግብ ጋር ያለውን መስተጋብር በሚመለከት ጥናት ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 11/2013 ( ኢዜአ) ኮቪድ-19 ከሥርዓተ ምግብ ጋር ያለውን መስተጋብር በሚመለከት የአንድ ዓመት ጥናት ለማካሄድ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ጥናቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚፈጥረውን የሕመም ስሜትና ልዩ ባህርያት ይዳስሳል።

እንዲሁም ከሥርዓተ ምግብ ጋር ካለው መስተጋብር ጋር በሕክምና ማገገሚያዎች ውስጥ ቆይታ በነበራቸው ታማሚዎች ላይ ክትትልና ጥናት በማድረግ መፍትሄዎችን እንደሚያስቀምጥ ተገልጿል።

በኢንስቲትዩቱ የቫይረስ ምርምር ዳይሬክተርና የጥናቱ አስተባባሪ ወይዘሮ ሳሮ አብዱላሂ እንደገለጹት፤ በመላ አገሪቱ ለአንድ ዓመት ያህል የሚካሄደው ጥናት በሽታውን የመከላከል አቅምና ስርጭት ለማየት ያስችላል።

ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ በቂ ዕውቀት ያልተያዘባቸውን ክፍተቶች ለመሙላት ታስቦ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።

በሽታው በህብረተሰቡ የአመጋገብ ሥርዓት የሚኖረው ተጽዕኖ እንደሚጠና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

በእርግዝናና በወሊድ ወቅቶች ላይ በሽታው ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ እንደሚዳሰስም አብራርተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት በ45 ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች ለሚካሄደው ጥናት 100 ሚሊዮን ብር  ተመድቧል ብለዋል።

ሚኒስቴሩም ለጥናቱ ውጤታማነት ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ 60 የሚሆኑ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የምርመራ ማዕከላት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።

በጥናቱ 20 የሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማትና አጋር የልማት ድርጅቶች ይሳተፋሉ።

በኢትዮጵያ ከ90 ሺህ በላይ ሰዎች   በኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን፤ ከ1 ሺህ 300 የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው ማለፉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ  ከ41 ሚሊዮን  በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል ።ከእነዚህ መካከልም  ከ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ  ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም