ቀጥታ፡

በዓሉ የህዝቦች እኩልነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያንፀባርቅ መልኩ ይከበራል... የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

አዳማ ፤ ጥቅምት 11/2013 (ኢዜአ) 15ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል እኩልነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያንፀባርቅ መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ አደም ፋራህ ገለጹ።

"እኩልነትና ህብረብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ  የሚከበረውን በዓል  በማስመልከት ምክር ቤቱ ከክልል ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ እየተወያየ ነው።

 አፈ-ጉባኤው  በውይይት መድረኩ እንደተናገሩት በዓሉ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ኩነቶች ይከበራል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነትና ባህል የሚያሳይ ባዛርና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እንደሚዘጋጅ አስታውቀዋል።

በዓሉ የህዝቦች እኩልነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚንፀባረቅበትም ነው ብለዋል።

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በዓሉን በተፈለገው መልኩ በአደባባይ በስፋት ወጥቶ ማክበር  ባይቻልም ሊኖር የሚችለውን ክፍተት ለመሙላት መገናኛ ብዙሃን ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

ከሊሂቃን፣ ሴቶችና ወጣቶች ጋር ሰፋፊ መድረኮች እንደሚኖሩም አስረድተዋል።

የእኩልነትና ህብረብሔራዊ አንድነት ችቦ ከጅግጅጋ ሲነሳ በሚያልፍበት ከተሞችና ክልሎች አቀባበል እንደሚደረግለት  ያመለከቱት አፈ- ጉባኤው  በትውልድ ቅብብሎሽ የዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባታ ከዳር ይደርሳል ብለዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች በሚያልፉበት ክልሎች የደም ልገሳ በማድረግ ኢትዮጵያዊያን በደም የተሳሰርን መሆኑን እናሳያለን ሲሉም ገልጸዋል።

በህዳሴው ግድብ ግንባታና የህዳሴ ዋንጫ አቀባበል ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እንደሚደረግም ተመልክቷል።

በአዳማ እየተካሄደ ባለው መድረክ ስለበዓሉ  አከባበር   መርሃ ግብር ለተሳታፊዎች  ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም