ወቅታዊ ስጋቶችን በመከላከል አገር የማሻገር ትውልዳዊ ተልእኮን መወጣት ይገባል - ዶክተር አብርሃም በላይ - ኢዜአ አማርኛ
ወቅታዊ ስጋቶችን በመከላከል አገር የማሻገር ትውልዳዊ ተልእኮን መወጣት ይገባል - ዶክተር አብርሃም በላይ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 11/2013 ( ኢዜአ) ለአፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ጆሮ ባለመስጠትና የተጋረጡ ወቅታዊ ስጋቶችን በመከላከል፣ ሰላምና መረጋጋትን ማስጠበቅና በልማት አገር የማሻገር ትውልዳዊ ተልእኮን መወጣት ይገባል ሲሉ ዶክተር አብርሃም በላይ ጥሪ አቀረቡ።
የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶክተር አብርሃም በላይ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለኢዜአ በላኩት መግለጫ እንዳሉት መላው ህዝብ የዜጎችን አብሮ የመኖር እሴትን በመናድ ህዝብን ከህዝብ መነጠል ዋነኛ ስራቸው አድርገው ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች በመጠበቅና ሴራቸውን በማክሸፍ ለአብሮነቱ ዘብ ሊቆም ይገባል።
ዶክተር አብርሃም በመግለጫቸው እንዳነሱት በአገሪቱ በተደረገው ለውጥ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚታይና አሳታፊ ለውጥ መጥቷል።
ይህ ያልተዋጠላቸውና አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለማፈራረስ የሚተጉ ኃይሎች አሁንም ህዝቡን እያዋከቡና እያጋጩ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
በተለይም በስሙ እየተነገደበት ያለው የትግራይ ህዝብ ከወንድም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመተባበር ነጻነቱን በብልሃት ማወጅ ይጠበቅበታል ብለዋል።
መላው የትግራይ ህዝብ በውጭ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆችና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመሆንና በጥበብና በማስተዋል ነገን በጋራ መገንባት ያስፈልጋል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
''ያለንበት የታሪክ ዘመን እጅግ ማስተዋልና የላቀ የአገር ባላደራነት የሚጠይቅበት’’ ነው ያሉት ዶክተር አብርሃም፤ "ወቅቱ አፍራሽ ሃይሎችን በተባበረ ክንድ የመደርመስ ስራ የሚሰራበት ነው" ብለዋል።
እንደ መግለጫው ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይም ከጥቂት ወራት ወዲህ ያጋጠሟትንና በመታገል ላይ ያለቻቸውን ጉልህ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎችን የመጋፈጥ ጉዳይ በቡድናዊ ውስን እይታ የፍላጎት መነፅርና፣ በቆሞ ቀር የአመለካከት ችንካር መፍትሔ የሚያገኝ አይደለም።
ከዚያ ይልቅ ከግብታዊነትና ቁንፅል አረዳድና እርምጃ ከፍ ብሎ የማሰብ፣ የህዝብ ፍላጎትንና ገዢ የህግ ማእቀፎችን በኃላፊነት አክብሮ የመጓዝ፣ የዚህን ትውልድ አገር የማሻገር ፈታኝ ታሪካዊ ተልእኮ በፅናት የመወጣት፣ በዚህም አገርን የማረጋጋትና የማስቀጠልን ዋና የጊዜውን ሚና መጫወትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
ዶክተር አብርሃም እንዳሉት "አፍራሽ ቡድኑ በህዝቦች መካከል መጠራጠርና አለመተማመንን ማንገስን እንደ ዋና የህልውናና በስልጣን የመቀጠል መርህ አድርጎ በመውሰድ ለረጅም ዘመን ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን ጠብቆ የኖረውን፣ ሐይማኖት፣ ዘርና ጎሳ ሳይለይ ዳር እስከዳር ተዋልዶ ተሳስቦና ተከባብሮ የኖረውን ህዝብ፣ ሰውሮ ባስቀመጠው የልዩነት ካርድ በመጠቀም ታሪክ ይቅር የማይለው ደባውን በሌላ ማልያ በማጫወት ከህዝብ የማይሰወር ተፈጥሯዊ የሴራ ፖለቲካውን ያለ ሀፍረት ቀጥሏል" ።
"ህዝባችን ከዚህ የዜሮ ድምር ታሪክ አጥፊ ጨዋታና የሞራል ዝቅታ በላይ ከፍ ብሎ ሴራዎቹን ይበጣጥሳል፤ በመላው የትግራይ ህዝብና የእውነተኛ የአገራችን የፌዴራሊዝም ሀይሎችና ታጋዮች የተለመደ አስተዋይነትና ትእግስት በህጋዊ ርምጃዎችና በህዝቦች የተባበረ ክንድ መልሱን ያገኛል" ሲሉም አክለዋል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከትግራይ ህዝቦች ጋር በመሰለፍ በተለያየ ጊዜ መንግስት የሚወስዳቸውን የተጠኑ ፖለቲካዊ እርምጃዎች በመደገፍና ለአፍራሽ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻቸው ጆሮ ባለመስጠት ከፊት የተጋረጡብንን ጉልህ የወቅቱ ስጋቶች መከላከል ይገባናል ብለዋል።
"የኮሮና ቫይረስ ስርጭትና የአንበጣ መንጋ የሚያደርሰውን ስጋት በመከላከል፣ የህዳሴ ግድባችን የማጠናቀቂያ ስራ ላይ መረባረብ፣ በአጠቃላይ አገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን የማስጠበቅ እና የተዘረጉ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ፕሮግራሞችን በንቃት በመደገፍና በመሳተፍ አገር የማስቀጠልና የማሻገር ትውልዳዊ ተልእኮአችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ" በማለት ዶክተር አብርሃም በላይ ጥሪ አስተላልፈዋል።