በጉጂ ዞን በመኸር ከ115 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጉጂ ዞን በመኸር ከ115 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው
ነገሌ ሀምሌ 9/2010 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ115 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ። በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ዘውዴ በቀለ እንዳስታወቁት እስካሁን በተካሄደው የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ ከ54 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዘር ተሸፍኗል። ከተዘሩት ዋና ዋና ሰብሎች መካከል ገብስ፣ ስንዴ፣ ባቄላ፣ አተርና በቆሎ ይገኙበታል ብለዋል። ልማቱም አዶላ፣ ሻኪሶ፣ ኡራጋን ጨምሮ በአምስት ወረዳዎች እየተካሄደ ሲሆን የዘር ሰራውም እስከ መጪው መስከረም ወር 2011 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል። ዘንድሮ በአጠቃላይ በመኸሩ ለማልማት ታርሶና ለስልሶ የተዘጋጀው መሬት ከአምናው በ7 ሺህ 294 ሄክታር ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል። የምርት ዘመኑን ለማስፈጸም በሞኤ ቦኮ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን አማካኝነት የቀረበው 50 ሺህ 793 ኩንታል ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል። በመኸር አዝመራውም ላይ አንድ ሺህ 531 ሴቶችን ጨምሮ ከ32 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው። ከልማቱ ተሳታፊዎች መካከል የቦሬ ወረዳ አበየ ቁጥሬ ቀበሌ አርሶ አደር ገመዳ ጎቡ ለዘር ስራ ካዘጋጁት ሶስት ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ግማሹን በበቆሎና ስንዴ ዘር ሸፍነዋል። የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ቀደም ብሎ በመቅረቡ ቀሪውንም ማሳ በባቄላ ምርጥ ዘር ለመሸፈን ማቀዳቸውን ተናግረዋል። በወረዳው የጉቱ ሬጂ ቀበሌ ነዋሪ ጂሎ ዱከሌ በበኩላቸው ለዘንድሮ መኸር እርሻ 30 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው ጥቅም ላይ እያዋሉት ነው። በምርት ዘመኑ በ2 ነጥብ 5 ሄክታር ይዞታቸው ላይ ከሚያለሙት ስንዴ፣ በቆሎ፣ ገብስና ባቄላ 48 ኩንታል ምርት ይጠብቃሉ። በጉጂ ዞን በ2010/2011 ምርት ዘመን 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።