ቀጥታ፡

ወደ ሩብና ግማሽ ፍጻሜ የሚያልፉ ቡድኖችን የሚለዩ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ሐምሌ 9/2010 ወደ ሩብና ግማሽ ፍጻሜ የሚያልፉ ቡድኖችን የሚለዩ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይካሄዳሉ። ነገ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ፋሲል ከተማ ከመከላከያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ሐሙስ ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም በሰበታ ስታዲየም ኢትዮ ኤሌትሪክ ከጅማ አባጅፋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይጫወታሉ። በሐዋሳ ስታዲየም ሐዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም የሚያያደርጉት ጨዋታ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ የሚደረግ ሲሆን የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚጫወት ይሆናል። በዕለቱ የሚደረጉት ጨዋታዎች መጀመሪያ መርሃ ግብር ወጥቶላቸው እንዲካሄዱ ተወስኖ የነበረው ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ቢሆንም የመርሃ ግብር ማስተካከያ ማድረግ በማስፈለጉ በአንድ ቀን መሸጋሸጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ፋሲል ከተማ ከመከላከያና ኢትዮ ኤሌትሪክ ከጅማ አባጅፋር መርሃ ግብሮች በአዲስ አበባና በጎንደር መካሄድ የነበረባቸው ቢሆንም በሁለቱ ከተሞች የሚገኙት ስታዲየሞች በዝናብ በመጨቅየታቸው ምክንያት ጨዋታዎቹ በክልል ከተሞች እንዲካሄዱ መወሰኑን ገልጿል። እስካሁን በጥሎ ማለፉ በሩብ ፍጻሜ አንድ ጨዋታ የተደረገ ሲሆን ሰኔ 14 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና አርባምንጭ ከተማን በመለያ ምት በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፉን ማረጋገጡ የሚታወስ ነው። በዝናብ ምክንያት ጨዋታዎችን ማድረግ አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ ቀጣይ የሐዋሳ ከተማና ሲዳማ ቡና አሸናፊ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ፤ እንዲሁም የግማሽ ፍጻሜ፣ የፍጻሜና የደረጃ ጨዋታዎች ከመስከረም 2010 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄዱ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ቀጣይ ጨዋታዎች ወደ ቀጣዩ ዓመት መሸጋገራቸው በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያካሂዳቸው ውድድሮች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው። የባለፈው ዓመት የጥሎ ማለፍ አሸናፊ ወላይታ ድቻ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ መሆኑ የሚታወስ ነው። የዘንድሮው የጥሎ ማለፍ ውድድር ከሚያዚያ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል። የ2010 የኢትዮጵያ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ የሚሆነው ክለብ በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ የሚሳተፍ ይሆናል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም