በኢትዮጵያ ያሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ወኪሎች የእንጦጦ ፓርክን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ያሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ወኪሎች የእንጦጦ ፓርክን ጎበኙ
አዲስ አበባ ጥቅምት 11/2013 (ኢዜአ) መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ወኪሎች የእንጦጦ ፓርክን ጎበኙ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባዘጋጁት የጉብኝት መርሃግብር መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እና የብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተገኝተዋል።
የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በኢትዮጵያ 47 ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውን አስታውሰው፣ "መገናኛ ብዙሃኑ አገራችንን ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ ጠቃሚ ሥራ እየሰሩ ይገኛል" ብለዋል።
የጉብኝቱ ዓላማ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑ በአገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገበውን ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንዲያውቁ ለማድረግ እንደሆነም ገልፀዋል።
እንደ ዶክተር ጌታቸው ገለጻ መርሃግብሩ ከጉብኝት ባለፈ ጋዜጠኞችን መረጃ ከሚያገኙበት ተቋማት በማስተዋወቅ በቀጣይ ዘገባቸው የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ ጭምር ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳድር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው "የጋዜጠኞቹ ጉብኝት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችውን ለውጥ በአግባቡ እንዲረዱ ለማድረግ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ጉብኝቱ ከአገር ግጽታ ግንባታ አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው ያመለከቱት።
በጉብኝቱ የተሳተፉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች በጉብኝቱ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ፓርኩ የሀገሪቱን የቱርዝም መዳረሻ ቁጥርና ገቢ ከፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ፓርኩ በአዲስ አበባ መገኘቱ ቱሪስቶች ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ጉዞ ለማድረግ ሲያስቡ እንደ ትራንዚት ለመጠቀም የሚያገለግል መሆኑንም ተናግረዋል።
ጎብኚዎች በፓርኩ ጉብኝት ሲያደርጉ የፓርኩን ደህንነት እና ንጽህና በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበትም የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ 47 ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመላ አገሪቱ ከ180 በላይ ባለሙያዎችን አሰማርተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ታውቋል።