ኢትዮጵያን እየተፈታተነ ያለውን የዋጋ ንረት ለማሻሻል እርምጃዎች መወሰድ ተጀምረዋል

83

አዲስ አበባ፣ ጥቅምቴ 10/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያን እየተፈታተነ ያለውን የዋጋ ንረት ለማሻሻል የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑ የኢፌዴሪ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በወቅታዊ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ከኮሚቴው አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል።

ኢትዮጵያን ካለፉት 10 ዓመታት ጀምሮ የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ተግዳሮች እያጋጠማት መሆኑም  ተገልጿል።

ለአገሪቷ የዋጋ ግሽበት ኢኮኖሚያዊና ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ምክንያቶች የተጠቀሱ ሲሆን ይህን ችግር በፖሊሲ ብቻ በአጭር ጊዜ ማስተካከል አዳጋች ነው ተብሏል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽነሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ እንዳሉት የአገሪቷን የዋጋ ግሽበት ለማስተካከል መዋቅራዊ ለውጦች ያስፈልጋሉ።

በኢትዮጵያ ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ባለፈ የተፈጥሮ ችግሮች ለዋጋ ግሽበቱ መባባስ አሉታዊ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የኢኮኖሚ ዕድገቱ ቀንደኛ ጠላት የዋጋ ንረት መሆኑን አንስተዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት መንግስት አገርበቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

እንደ ዶክተር እዮብ ገለጻ ከብሄራዊ ባንክ በቀጥታ የሚወሰድ ብድር ኢኮኖሚ ውስጥ ያልነበረን ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚ በማስገባት የዋጋ ንረቱን የሚያባብስ ነው።

ይህን ችግር ለመፍታት በተለይ በ2013 ሩብ ዓመት 33 ቢሊዮን ብር በላይ የግምጃ ቤት ሰነድ መግዛቱን አስታውቀዋል።

የገንዘብ ኖት ቅያሪው የዋጋ ንረቱን በማስተካከል በኩል መልካም ውጤት እያሳየ መሆኑን የገለጹት ዶክተር እዮብ ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።

የብር ቅያሪው ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ከመከላከል ባለፈ የፋይናንስ ስርዓቱን በማዘመን በኩልም ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም