ምክር ቤቱ `ለሚ ኩራ`ን የአዲስ አበባ 11ኛ ክፍለ ከተማ በማድረግ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ `ለሚ ኩራ`ን የአዲስ አበባ 11ኛ ክፍለ ከተማ በማድረግ አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት10/2013(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት "ለሚ ኩራ"ን 11ኛ ክፍለ ከተማ አድርጎ አጸደቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቱ 8ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በዛሬ የከሰዓት ውሎው ክፍለ ከተሞችንና ወረዳዎችን እንደገና ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።
በአዲሱ አደረጃጀት የነዋሪዎችን ብዛት በማመጣጠን የአገልግሎት ተደራሽነትና የማስተዳደር አቅምን በማጎልበት ለከተማው ነዋሪዎች ሚዛናዊ በሆነ ርቀት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል።
በተጨማሪም አደረጃጀቱ የአገልግሎት አቅርቦትን በማመቻቸት ነዋሪዎች ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚረዳ መሆኑንም ተመልክቷል።
አዲሱ ክፍለ ከተማ ተጨማሪ ይዞታ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ከነበረው ከቦሌ እና ከየካ ክፍለ ከተሞች የነበሩ አንዳንድ ወረዳዎችን በመክፈል የተዋቀረ መሆኑም ተገልጿል።
ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ 9 ወረዳዎች ያሉት ሲሆን ከቦሌ እና ከየካ ክፍለ ከተሞች ባሉ አዋሳኝ ወረዳዎች የተዋቀረ ነው።
ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ያደረገ ሲሆን ክፍለ ከተሞችን እና ወረዳዎችን ዳግም የማቋቋሚያ አዋጁን በ3 ድምጸ ታዕቅቦና በአንድ ተቃውሞ አወጅ ቁጥር 72/2013 ሆኖ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።
በከተማው በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ባሉ ወረዳዎች በተደረገ ሽግሽግ 14 አዳዲስ ወረዳዎች እንደተፈጠሩም ለማወቅ ተችሏል።
በዚህም ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የአዲስ አበባ 11ኛው ክፍለ ከተማ እንዲሆን ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው ወስኗል።