የፖለቲካ ፓርቲዎችና መገናኛ ብዙኃን ለሰብዓዊ መብት መከበር በኃላፊነት እንዲሰሩ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎችና መገናኛ ብዙኃን ለሰብዓዊ መብት መከበር በኃላፊነት እንዲሰሩ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብት መከበር የፖለቲካ ፓርቲዎችና መገናኛ ብዙኃን ኃላፊነትን ተላብሰው ድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በኢትዮጵያ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታና በተቋማት ሚና ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከመገናኛ ብዙኃን አካላት ጋር እየተወያየ ነው።
በውይይቱ መገናኛ ብዙኃንና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰብዓዊ መብት መከበር ላይ ያላቸውን ሚና የሚዳስሱ ጽሁፎች ቀርበዋል።
የሕግና ሚዲያ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ጎሹ መገናኛ ብዙኃን ለሰብዓዊ መብት መከበር እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች "ሰብዓዊ መብትና የመገናኛ ብዙኃን ሚና በኢትዮጵያ"በሚል ርዕስ አቅርበዋል።
መገናኛ ብዙኃን መንግሥት ሰብዓዊ መብትን ለማስከበር የሕግና ተቋማዊ አደረጃጀቶችን ለማሻሻል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አፈጻጸም ተከታትሎ በመዘገብ ክፍተት አለባቸው ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት መርሆዎችንና ባህሪያትን ተረድቶ ከመሥራት አኳያም ጉድለቶች እንደሚታዩ ገልጸዋል።
ከሆነ መገናኛ ብዙኃን ለመብቶች መከበር እንደሚሰሩ ቢጠበቅም፤ የተወሰኑት ብሔር ተኮር ግጭቶችን ከመዘገብ የራሳቸው አጀንዳ በማራመድ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ይዘግባሉ።
አገሪቱ በምትገኝበት የፖለቲካ ሽግግር ብዝኃነትን በማስተናገድ፣ ወገንተኛ ባለመሆን፣ ነጻና ገለልተኛ ሆነው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ኃላፊነትን በተላበሰ ሁኔታ እንዲያስተናግዱም መክረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰብዓዊ መብት አከባበር ያላቸው ሚናን በሚመለከት ጽሁፍ ያቀረቡት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ዮናስ አሽኔ ናቸው።
በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰብዓዊ መብትን በመርሃ ግብራቸውና በመግለጫቸው የሚያስተናግዱበትን ሁኔታ አስቀምጠዋል።
አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች በመርሃ ግብራቸው(ማኒፌስቶ) የሰብዓዊ መብት እሴቶችንና ይዘትን ቢያስገቡም፤ በሚያወጧቸው መግለጫዎች ብሔር ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
ፓርቲዎቹ በሰብዓዊ መብቶች በጋራ የሚሰሩባቸው ሁኔታዎችን በመፍጠር የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማውገዝና ንቅናቄ በማድረግ በኃላፊነት እንዲሰሩ ምክር ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አምሃ መኮንን በበኩላቸው ተቋሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተፈጸሙበት ሥፍራድረስ በመሄድ እንደሚያረጋገጥና ከመንግሥት ወገን የሚሰጠውን ምላሽ እንደሚመረምሩ ተናግረዋል።
"ሁሉም ሰው በሰውነቱ እንዲከበር የመገናኛ ብዙንና የፖለቲካ ፓርቲ ተዋናዮች ሚናቸው ከፍተኛ ነው" ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የብሔር ግጭቶችን ለማስቀረት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ከመገናኛ ብዙኃን እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የሚሰሩት ዘገባዎች ኃላፊነት በተሞላውና አስተማሪ በሆነ መንገድ መቅረብ ይገባቸዋል።