ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የመስህብ ሀብቶቿን በአግባቡ መጠበቅና ማስተዋወቅ ይገባታል

ሀዋሳ፣ ጥቅምት 10/2013 (ኢዜአ ) ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን የመስህብ ሀብቶቿን በአግባቡ መጠበቅና ማስተዋወቅ እንደሚገባት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ።

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የስንቅሌ ቆርኬዎች መጠለያን ጎብኝተዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የቱሪዝም ኢትዮጵያ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በወቅቱ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሀይማኖታዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች ባለቤት ናት።

"ይሁን እንጂ መስህቦችን በአግባቡ ጠብቆ ለጎብኝዎች ከማስተዋወቅ አንጻር በተገቢው መንገድ አልተሰራም" ብለዋል።

ሀገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን የመስህብ ሀብቶቿን መጠበቅና ማስተዋወቅ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

"የመስህብ ስፍራዎችን ለጎብኝዎች ከማስተዋወቅ አንጻር በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ጋዜጠኞች እያደረጉ ያለው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም " ሲሉም ተናግረዋል።

የኦሮሞ አባገዳዎች የስንቅሌን የቆርኬዎች መጠለያ በገዳ ስርዓት እንዲጠበቅ ያደረጉት ምርጥ ተሞክሮ አካባቢው ጉዳት እንዳይደርስበትና የቆርኬዎች ቁጥር እንዲጨምር ያስቻለ በመሆኑ ሊበረታታ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተለያዩ ሀገራት ያሉ ፓርኮችን ተዘዋውረው እንደጎበኙ የተናገሩት አቶ ኃይለማርያም ኢትዮጵያ በመስህብ ሀብቶቿ ከሌሎች የተሻለች ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

"ይሁንና የመስህብ ሀብቶቿን ከማስተዋወቅ አንጻር ያለው ክፍተት በሚገባት ልክ እንዳትታወቅ አድርጓታል" ብለዋል ።

በተወሰኑ የቱሪዝም ዘርፎች በጋዜጠኞች እየተሰራ ያለው ስራ ብቻውን ውጤት ስለማያመጣ ተሞክሮውን  አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመላክተዋል።

የመስህብ ሀብቶችን በተገቢው መንገድ አልምቶና ጠብቆ ለጎብኝዎች በማስተዋወቅ የድርሻቸውን ለመወጣት በማሰብ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ጋር በመሆን ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽንን በማቋቋም ወደ ስራ እንደገቡ  አስታውቀዋል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው መንግስት የመስህብ ስፍራዎችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ የተለያዩ ተግባራትን እያከነወነ መሆኑን ተናግረዋል ።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በመሪነታቸው ወቅት ያቋቋሙትን የቱሪዝም ኢትዮጵያን በቦርድ ሰብሳቢነት እያደረጉ ካለው እገዛ በተጨማሪ በፋውንዴሽናቸው በኩል ለዘርፉ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

"የኢትዮጵያን ሀብት ለማስተዋወቅ በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል" ያሉት ደግሞ  የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ናቸው።

"በነዚህ ውስን አካላት የተሰራው ስራ ቀላል ዋጋ የማይሰጠው አይደለም" ያሉት አቶ ኩመራ ባለሙያዎቹና ጋዜጠኞቹ ዘርፉን ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።

ከጉብኝቱ ጎን ለጎን "የሚዲያዎች ሚና ለቱሪዝም ዘርፍ ሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ የብዙሀን መገናኛ አካላትም በጉብኝቱ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም