በመስከረም ወር ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ጭማሪ አሳይቷል... የጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በመስከረም ወር ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ጭማሪ አሳይቷል... የጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ምርመራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተደረጉ የላቦራቶሪ ምርመራዎች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የመስከረም ወር ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኢትዮጵያ የኮቪድ19 ስርጭት ያለበት ሁኔታ፣ ቫይረሱ በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የተሰጠው ምላሽና በቀጣይ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ ገለጻ ተደርጓል።
በገለጻው የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት በአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ስጋት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ህብረተሰቡ በአግባቡ ሊረዳ ይገባል።
ቫይረሱ በአገሪቱ ከተገኘበት ጊዜ አንስቶ ከተደረጉ የላብራቶሪ ምርመራዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር የባለፈው መስከረም ወር በከፍተኛ ሁኔታ የመጨመር አዝማሚያ ማሳየቱን ተናግረዋል።
"ይህ ደግሞ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ያስገነዘበ ነው" ብለዋል።
እንደሚኒስትሯ ገለጻ፣ ባለፉት ጊዜያት በተደረገ ያላሰለሰ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ በሽታው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ተችሏል።
"ነገር ግን ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲከፈቱ ውሳኔ ላይ መደረሱን ተከትሎ የሰዎች መዘናጋት እየጨመረ መምጣቱ ተስተውሏል" ብለዋል።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የቫይረሱ ስርጭት መጨመሩን እንጂ መቀነሱን የሚያሳዩ መረጃዎች እንደሌሉ ህብረተሰቡ ተረድቶ ራሱንና ቤተሰቡን ከቫይረሱ እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
"በተለይ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩ ስለ ኮሮናቫይረስ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ እራሳቸውን እንዲከላከሉ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አለባቸው" ብለዋል።
እንደ ዶክተር ሊያ ገለጻ በኢትዮጵያ እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ከ1 ሚሊዮን 383 ሺህ በላይ ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን 87 ሺህ 834 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል፤ 1ሺህ 337 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ ባቀረቡት ጽሁፍ በአገሪቱ የምርመራ መጠን ቢቀንስም ቫይረሱ የሚገኝባቸውና ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በተቃራኒው እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።
በኮቪድ-19 ከሚያዙ ሰዎች ውስጥ 14 ነጥብ 9 በመቶዎቹ ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል እንደሚገቡም አቶ አስቻለው ጠቁመዋል።
"እየታዩ ያሉ መረጃዎች የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት ከምጊዜውም በላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን የሚያሳዩ ናቸው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በበኩላቸው ኮቪድን ለመከላከል በእጃችን ያሉ መፈትሄዎችን አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ወላጆች፣ የመንግስትና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች አካላት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ይህ ካልሆነ ግን ቫይረሱ የሚያደርሰው ተጽእኖ ቀላል እንደማይሆን ነው ያስታወቁት።
ባለፉት ወራት ኮሮናቫይረስን ለመከላከል በተደረገው ጥረት በቀጣይ ለጤናው ዘርፍ የሚጠቅሙ መልካም ተሞክሮዎች ተሰንቀዋል።
"በሽታን ለመከላከል ቀድሞ መዘጋጀት፣ በእጅ ያሉ አቅሞችን አሟጦ መጠቀም፣ አጋር ድርጅቶችን ማቀናጀትና የህብረተሰብና የተቋማት ድጋፍን መጠቀም ውጤት እንደሚያስገኝ ተገንዝበናል" ብለዋል።
እስካሁን ኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደረገው ርብርብ ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ በቀጣይ ከእስከዛሬው የበለጠ ሥራ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
የተቋማት ሥራ ኃላፊዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች ቫይረሱን በመከላከል በኩል አርአያ መሆን እንዳለባቸውም ነው ያመለከቱት።
በኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ቡሬማ ሃማ እንዳሉት ኢትዮጵያ ኮቪድን ለመከላከል እያደረገች ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው።
በቀጣይ ትምህርት ቤቶችን ለመክፍት የተጀመረው ጥረት በጥንቃቄ መከወን ይገባዋል ብለዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።