የሶፍ ኡመር ዋሻን በማልማት ለቱሪዝም ምቹ ማድረግ ይገባል- ጎብኝዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሶፍ ኡመር ዋሻን በማልማት ለቱሪዝም ምቹ ማድረግ ይገባል- ጎብኝዎች

ጎባ፣ ጥቅምት 9/2013 (ኢዜአ) በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኘውን የሶፍ ኡመር ዋሻ በማልማት ለቱሪዝም ምቹ ማድረግ እንደሚገባ ጎብኝዎች ገለጹ።
ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ጎብኝዎች የሶፍ ኡመር የተፈጥሮ ዋሻን ጎብኝተዋል፡፡
ከጉጂ ዞን የመጡ ወይዘሮ አንለይ ኃይለጊዮርጊስ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በቴሌቪዥን ያዩትን የሶፍ ኡመር ዋሻን በአካል ተገኝተው በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።
ሆኖነም ዋሻው የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ ቢሆንም በአካባቢው የመንገድ፣ የኤሌክትሪክና ሌሎች የመሰረተ ልማቶች የተሟሉለት አለመሆኑን መታዘባቸውን ተናግረዋል።
ወይዘሮ አንለይ በአካባቢው የመሰረተ ልማት አለመሟላት ጎብኝዎች በሚፈለገው ልክ ወደ አካባቢው እንዳይመጡ የሚያደርጋቸው መሆኑን ጠቅሰዋል የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አቶ ቱራ ታምሩ የተባሉ ጎብኚ በበኩላቸው የሶፍ ኡመር ዋሻ ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ አቅም ያለው ቢሆንም በአካባቢው ያለው የመንገድ፣ የማረፊያና ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግር ለጎብኝዎች አስቸጋሪ እነደሆነ ተናግረዋል::
የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ መንግስትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ቱራ ጠቁመዋል።
"በዞኑ ሶፍ ኦመር ዋሻን ጨምሮ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች መኖራቸውን በጉብኝቴ ተገንዝብያለሁ" ያሉት ደግሞ አቶ ሊበን ሀለኬ ናቸው።
በተለይም በሶፍኡመር ዋሻ መዳረሻ ከፍተኛ የሆነ የመንገድ ችግር መኖሩን ጠቁመው ስፍራውን በማልማት ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የምስራቅ ባሌ ዞን የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ማማ በዞኑ የሚገኙ የቱርስት መስህብ ስፍራዎችን በማልማት ለገቢ ምንጭነት ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጓዳኝ ዋና ዋና መስህቦችን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መዝገብ ላይም በቋሚነት እንዲሰፍሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ሶፍ ኡመር የተፈጥሮ ዋሻ፣ ድሬ ሼህ ሁሴን ጥንታዊ መስጅድ፣ ሶፍ ኡመር ሀመራ፣ መካነ መቃብር፣ የእደ ጥበብ ሥራዎች፣ ከኦሮሞ ህዝብ የትግል ታሪክ ውስጥ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው የጎኒ ተራሮችን ጨምሮ ሌሎችም የቱሪስት መስህቦች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደም ቃሲም በዞኑ የሚገኙ የቱርስት መስህብቦች በሚፈለገው ደረጃ ከለሙ የአገር ኢኮኖሚን በመደገፍ ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡
መንግስት በዞኑ የሚገኘውን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት መስህቦቹን የማልማትና የማስተዋወቅ ሰራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሶፍ ኡመር የተፈጥሮ ዋሻ በአዲሱ ባለ መቶ ብር ላይ መታተሙና ከሮቤ- ወደ ሶፍ ኡመር የሚወስደውን መንገድ ወደ አስፈልት ደረጃ ለማሰደግ የዲዛይን ስራ መጠናቀቅን በመሳያነት ጠቅሰዋል።
በምስራቅ ባሌ ዞን ውስጥ የሚገኙ የሶፍ ኡመር የተፈጥሮ ዋሻና የድሬ ሼህ ሁሴን ጥንታዊ መስጂድ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መዝገብ ላይ በጊዜዊነት መስፈራቸውን ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡